በ6 ወራት ከ3 ሺሕ 400 በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራ መደረጉን ኤጀንሲው አስታወቀ

የካቲት 7/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ በ2014 በጀት ዓመት 6 ወራት ብቻ ከ3 ሺሕ 400 በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራ መደረጉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) የሳይበር ደኅንነት ጥቃትን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ የመጀመሪያው ጥቃት የመሰረተ ልማቶች ቅኝት ላይ መደረጉን አስታውቀው በተቋማት የሀርድና የሶፍት ዌር መጠቀሚያ መሰረተ ልማቶች ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በግማሽ በጀት ዓመቱ ባንኮች፣ ኢንሹራንሶች፣ ማይክሮ ፋይናንስ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች ዒላማ ሆነው እንደነበርም ጠቁመዋል።

በሁለተኛ ደረጃ በድረገፆች ላይ የጥቃት መድረሱን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ ስምንት የሚደርሱ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሳይበር ጥቃት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል፡፡

የሳይበር ደኅንነት ጥቃትን ለመከላከል የሳይበር ደኅንነት ሥነምህዳር ህጎችን የመጠበቅና የማስጠበቅ የሁሉም ተቋማት ኃላፊነት እንደሆነም ተናግረዋል።

ሚዲያዎችም የሳይበር ደኅንነትን ለማስጠበቅ ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል፡፡

በሱራፌል መንግስቴ