በ8.3 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ

ግንቦት 9/2014 (ዋልታ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ካፋ ዞን ጠሎ ወረዳ 8 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገበት የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተመረቀ።
ግንባታው በ8 ወራት የተጠናቀቀውን ፕሮጀክት የክልሉ መንግሥት ዋና ተጠሪ ፀጋዬ ማሞ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
የመንግሥት ዋና ተጠሪው ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ የሕዝቡን ጥያቄ በዘላቂነት ሊፈታ የሚችል መሆኑን ገልጸው በቀጣይ መንገድን ጨምሮ ሌሎች በአካባቢው የሚስተዋሉ የመሰረተ ልማች ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት መንግሥት በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እንዳሻው ከበደ በበኩላቸው በሕዝብ መድረክ ሲነሱ ከነበሩት ጥያቄዎች አንዱ የመጠጥ ውሃ እንደነበር አስታውሰው የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የተያዙ ዕቅዶች ደረጃ በደረጃ እየተከናወኑ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ ሚሊዮን ኃይሌ የሕዝቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ጥያቄ ለዘመናት የዘለቀ መሆኑን ጠቁመው ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ላስቻሉ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ፕሮጀክቱ ዋን ዋሽ ፕሮግራም በመደበው 8 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን ከ2 ሺሕ 400 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ያገለግላል መባሉን የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ የላከልን መረጃ አመላክቷል።