ባለሥልጣኑ የሃይማኖት ብሮድካስት ረቂቅ መመሪያ ዙርያ ተወያየ

መጋቢት 22/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሃይማኖት ብሮድካስት ረቂቅ መመሪያ ዙርያ ውይይት አደረገ።

የውይይቱ ዓላማ የሃይማኖት ብሮድካስት አገልግሎት ፈቃድ አሰጣጥ ሂደት ግልፅ እና  ፍትሃዊ ለማድረግ፣ የሃይማኖት ብሮድካስት ጣቢያዎችም ሃይማኖታዊ ሚናቸውን በተገቢው መንገድ እንዲጫወቱ ለማስቻል እንዲሁም ከሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ጋር በረቂቁ ዙርያ የተለያዩ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሐመድ እድሪስ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ለኅብረተሰቡ በተለይም ለእምነቱ ተከታዮች ተደራሽ በመሆን ሃይማኖታዊ አስተምሯቸውን ከማድረስ ጎን ለጎን አብሮነትን፣ መረዳዳት፣ እህትና ወንድማማችነት፣ ሰላም፣ ፍቅርና መሰል የሁሉም ሃይማኖቶች እሴት የሆኑትን ተግባራት በኅብረተሰቡ ዘንድ ማስረፅ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

መመሪያው ለውይይት የቀረበው ግብዓት ለማሰባሰብ እንደሆነ እና ቦርድ ሲቋቋም የሚፀድቅ መሆኑን አክለው መግለጻቸውን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡