ባለስልጣኑ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሠራ ገለጸ

ሰኔ 2/2014 (ዋልታ) የኢፌዴሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማ እና ሁሉን አሳታፊ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሠራ ገለጸ፡፡

እንደ ሀገር የተያዙ የብልፅግና መንገዶች ማኅበረሰቡን በሁሉም አቅጣጫ ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችሉ ባለስልጣኑ እየሠራ መሆኑ ተመላክቷል።

የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም የክትትል ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸው ነው የተነገረው፡፡

የባለስልጣኑን ኃለፊነት በሚመለከት አዲስ ረቂቅ አዋጅ ፀድቆ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን የሕዝቡን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚችል መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በዚህም 2 ሺሕ 50 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከለውጡ ወዲህ ተመዝግበው ወደ ሥራ መግባታቸው ተገልጿል።

ከመንግሥት እና ከተለያዩ አካላት የሚመጡ ጥቆማዎችን መሰረት በማድረግ በባለስልጣኑ የተመዘገቡት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምን እየሠሩ እንደሆነ የክትትል ሥራ በባለስልጣኑ እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡

በአጠቃላይ ተቋሙ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራር ትምህርት ወስዶ በዋናነት የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ላይ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑ ነው የተመላከተው::

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማ እንዲሆን ማኅበረሰቡ እና የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምክክር መድረኩ ውጤታማነት አበርክቶ እንደኖራቸው ለማድረግ የንቅናቄ መድረኮችን በማዘጋጀት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እንደሚሠራ ነው ያስታወቀው።

በተጨማሪም ሀገራዊ ምክክር መድረኩ ፍትሐዊ እና ሁሉን አሳታፊ መሆኑን እንደሚከታተል አስታውቋል፡፡

በሜሮን መስፍን