ባለስልጣኑ በቡና ኤክስፖርት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታወቀ

መስከረም 5/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን በቡና ኤክስፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታወቀ።

በቡና ምርት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት እንዲኖራት በማድረግ አስተዋጽኦ ላደረጉ የቡና አምራች አርሶ አደሮች፣ ላኪዎች እና አቅራቢዎች የእውቅና አሰጣጥ መርኃ ግብር እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ከ300 ሺሕ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ በመላክ ነው 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር መገኘቱ የተገለፀው።

ይህ ውጤት በቡና ምርት ለማግኘት የተፈለገውን ውጤት ከማሳካትም በላይ እንደ ሀገር የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ በእጅጉ የሚያፋጥን ነው ተብሏል።

የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን ኢትዮጵያ የተሻሻለ የግብርና ሥርዓት በመከተሏ በዘርፉ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

የሚኒስቴሩ ቀጣይ አቅጣጫዎች አንዱ የቡና ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

በመርኃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲስ እና የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ተገኝተዋል።

በሜሮን መስፍን