ባለስልጣኑ የአቅመ ደካሞችን ቤት እደሳ መርኃ ግብር አካሄደ

ሰኔ 19/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤት እደሳ መርኃ ግብር በጉለሌ ክፍል ከተማ አካሄደ።

ባለስልጣኑ በከተማ ደረጃ 121 ቤቶችን ለማደስ እቅድ ይዞ እየተገበረ እንደሚገኝም ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ባለሙያዎችና አመራሮች ገንዘብ በማዋጣትና በማሰባሰብ የበጎ አድራጎት ሥራውን እንደሚሰሩም ተጠቁሟል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማም 10 የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶችን ለማደስ በተያዘው እቅድ መሰረት ወደ ሥራ ተገብቷል።

የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ደንብ ሲባል የህግ ጥሰቶችን የሚከላከልና ህገ ወጥ ቤቶችን አፍራሽ ተደርጎ በኅብረተሰቡ እንደሚሳል ገልጸው ይሁን እንጂ በጎ ሥራዎችን በመስራት የኅብረተሰቡ አለኝታነታችንን ማረጋገጥ እንፈልጋለን ብለዋል።

የደንብ ማስከበር በክረምት በጎ ፍቃድ መርኃ ግብር በአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤት እደሳ፣ በደም ልገሳ፣ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርና መሰል የበጎ አድራጎት ሥራዎች እየተሳተፈ ነው ተብሏል።

ባለስልጣኑ አሳዳጊ የሌላቸው 72 ህጻናትን እንደሚረዳም ተገልጿል።