ባንኩ ለ1 ሺህ ቤተሰቦች የኢፍጣርና የማዕድ ማጋራት መርሃ-ግብር አካሄደ

ሚያዚያ 19/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ኑር ከባቡል ኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በመተባበር ለ1 ሺህ ቤተሰቦች የኢፍጣርና የማዕድ ማጋራት መርሃ-ግብር አካሄደ፡፡

ባንኩ ቤተሰቦችን በመመገብና ቁሳቁስን በመለገስ እንዲሁም ችግረኞች ራሳቸውን እንዲችሉ የሙያ ስልጠና እና ድጋፍ በመስጠት በሚታወቀው የ’ባቡል ኸይር’ የበጎ አድራጎት ድርጅት ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው የኢፍጣርና የማዕድ ማጋራቱን ያከናወነው፡፡

በስነ ስርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቢኢ ኑር ምክትል ፕሬዝዳንት ኑሪ ሁሴን እንደተናገሩት ባንኩ በዚህ የረመዳን ወር በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ በማድረግ የኢፍጣርና የማዕድ ማጋራት መርኀ-ግብሮችን በ9 የተለያዩ ከተሞች ለ10 ሺህ ቤተሰቦች በማካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ለተከታታይ ቀናት ተመሳሳይ መርኀ-ግብሮች እንደሚቀጥሉና በአጠቃላይ በ‘ባቡል ኸይር’ አማካይነት ለ5 ሺህ ቤተሰቦች የኢፍጣርና የማዕድ ማጋራት መረኀ-ግብሮች እንደሚከናውኑ ተገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ባንኩ በ14 ከተሞች ከ2 ሺህ 500 በላይ ደንበኞች ጋር በመሆን የኢፍጣር ዝግጅት እያካሄደ መሆንኑ ተናግረዋል፡፡

በመርኀ-ግብሩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ኤፍሬም መኩሪያ በበኩላቸው ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸው በቀጣይ ጊዜያትም ይህን ኃላፊነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን የባንኩ መረጃ ያመለክታል፡፡