ታኅሣሥ 12/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያዘጋጀው የ”ይመንዝሩ፣ ይቀበሉ፣ ይሸለሙ” የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማበረታቻ የእጣ ማውጣት መርኃግብር ተካሄደ።
የ23ኛው ዙር የሽልማት ስነ ሥርዓት በህገወጥ መልኩ የሚገባውን ብሎም የሚመነዘረውን የውጭ ምንዛሬ ህጋዊ በማድረግ የምንዛሬ ግኝትን ለማበረታታት የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማዕከላዊ ሪጅን ምክትል ፕሬዝዳንት ኪዳኔ መንገሻ የአገሪቱን ልማት በሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ የሀብት ማሰባሰብ በተለይም የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማሳደግ አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
ባንኩ በይመንዝሩ፣ ይቀበሉ፣ ይሸለሙ መርኃግብሩ ከ52 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሽልማቶችን ለደንበኞች መሸለሙ ተገልጿል።
በ2013 የበጀት ዓመት የጥቁር ገበያ ምንዛሬ ሂደት እና የኮቪድ-9 ወረርሽኝን በመቋቋም ከ2 ነጥብ 64 ቢሊየን በላይ የአሜሪካ ዶላር መሰብሰብ መቻሉ የተገለፀ ሲሆን የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ወደ አገራቸው የሚገቡ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኙ ለማድረግ ባንኩ ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ታውቋል።
በ23ኛው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የይመንዝሩ፣ ይቀበሉ፣ ይሸለሙ መርኃግብር አንደኛ እጣ ዘመናዊ የቤት መኪና ተሸላሚ የሆኑት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሀይቅ ቅርንጫፍ ደንበኛ ሲሆኑ ቁጥሩም 8195672 ሆኖ ወጥቷል።
በቁምነገር አሕመድ