ብሔራዊ ባንክ የመመስረቻ መስፈርቱን ላሟሉ ስምንት ባንኮች ፈቃድ ሰጠ

ሰኔ 1/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የመመስረቻ መስፈርቱን ላሟሉ ስምንት አዳዲስ ባንኮች ፈቃድ መስጠቱን አስታወቀ።

በብሔራዊ ባንኩ የባንክ ቁጥጥር ዳይሬክተር ፍሬዘር አያሌው በፋይናንስ ዘርፉ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ለውጦችን ተከትሎ በርካታ ባንኮች የመመስረቻ ፈቃድ ለማግኘት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም ባንክ ለመመስረት የሚያስፈልገው ዝቅተኛ የካፒል መጠንን ከ500 ሚሊዮን ወደ 5 ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረጉን አስታውሰው አጠቃላይ መስፈርቱን ላሟሉ ፈቃድ እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህ መሰረት የመመስረቻ ፈቃድ ከጠየቁ 25 አዳዲስ ባንኮች መካከል ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን መስፈርት አሟልተው ለተገኙ ስምንት ባንኮች ፈቃድ መስጠቱን ተናግረዋል።

በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ ካገኙ ስምንት ባንኮች በተጨማሪ ሦስት ባንኮች ፈቃድ የማግኘት ሂደቱን እያጠናቀቁ ሲሆን ሦስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንደሚያገኙ ገልጸዋል።

ብሔራዊ ባንክ ከቅድመ ማመልከቻ ሂደት ጀምሮ ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ገልጸው የምስርታ ሂደቱ ካልተሳካ ለባለአክሲዮኖች ገንዘባቸው ተመላሽ ይሆናል ብለዋል።

በተመሳሳይ አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ወደ ባንክ እንዲሸጋገሩ በ2012 ዓ.ም ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመሪያ መሰረት መስፈርቱን ያሟሉ ሦስት አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ወደ ባንክ መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።

ሌሎች ሁለት አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት ደግሞ መስፈርቱን አሟልተው ፈቃድ ለማግኘት በሂደት ላይ ናቸው ብለዋል።

የባንክ ዘርፉ በአሁኑ ወቅት ከ120 ሺሕ በላይ ዜጎች ቀጥተኛ የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን አዳዲስ ባንኮች ወደ ዘርፉ መምጣታቸው አማራጭ አገልግሎትን ከማቅረብና የሥራ እድል ከመፍጠር አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እስካሁን ለ28 ባንኮች ፈቃድ መስጠቱ ታውቋል፡፡