ብሔራዊ የዲጅታል ክፍያ ስትራቴጂ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው

ሐምሌ 08/2013 (ዋልታ) – ብሔራዊ የበይነ መረብ (ዲጅታል) ክፍያ ስትራቴጂ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በመድረኩ የብሔራዊ ባንክ አመራር አባላት የተባበሩት መንግስታት የልማት የካፒታል ፈንድና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

የብሔራዊ ባንክ የክፍያ ስርዓትና ሴትልመንት ዳይሬክተር  ማርታ ሀይለማርያም  የዲጅታል ክፍያ አገልግሎት ከግለሰብ ጀምሮ እስከ መንግስት ባሉ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የሚጫወተው ሚና ጉልህ ነው ብለዋል።

የዲጅታል ክፍያ አገልግሎት በአገራችን በጅምር ላይ መሆኑን ተናግረው ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ክፍያን በቀላል፣በአነስተኛ ወጪ እና ጊዜ አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለመፈፀም ይረዳል ነው ያሉት፡፡

የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን እርካታ መጨመር እና የዘርፉን ተወዳዳሪነት በማሳደግ  ለአገራዊ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አንስተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።