ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ሕገ-ወጥ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሚኒስቴሩ አሳሰበ

ግንቦት 16/2014 (ዋልታ) የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ሕገ-ወጥ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳሰበ።
ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት በዚህ ወቅት ከዚህ ጥብቅ ትሥሥር እና ቁርኝት ውጪ ልሁን የሚል አካል የለም ያለው ሚኒስቴሩ ዓለማችንን በጥብቅ ትሥሥር ውስጥ እንድትቆይ ከሚያስገድዷት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ንግድ እንደሆነ ጠቁሟል።
በዚህ ትሥሥር ውስጥ መቆየት የሚቻለው የንግድ ሥርዓት በጥሩ ዲሲፒሊን ሲመራ ብቻ እንደሆነ ጠቁሞ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ከሀገር እና ከሰፊው ሕዝብ ተጠቃሚነት በተጻረረ መልኩ የግል ጥቅማቸውን ብቻ ለማረጋገጥ ጥረት የሚያደርጉ ሕገ-ወጥ አካላት መበራከታቸውን ገልጿል።
ይህም በሀገራችን የተረጋጋ የኢኮኖሚ ፍሰት እንዳይኖር ማድረጉን አውስቷል።
ሚኒስቴሩ የሀገራችንን የግብይት ሥርዓት ዘመናዊ እና በውድድር ላይ የተመሠረተ በማድረግ የሀገሪቱን እና የሕዝቡን አንጻራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ገልጿል።

መንግሥት እየተስተዋለ ያለው የሸቀጦች ዋጋ ንረት በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ በሚገኙ ዜጎች ላይ የሚፈጥረውን ጫና ለማቃለል መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦችን ከውጪ በፍራንኮ ቫሉታ እና ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ አድርጓል።

በዚህ መንገድ የሚገቡት ምርቶች ግን ለታለመላቸው ዓላማ ከመዋል ይልቅ ለተወሰኑ ሕገ-ወጥ አካላት የኪስ ማድለቢያ ሲሆኑ እየታየ ነው ብሏል፡፡

ይህንን ያልተገባ ድርጊት ለማስቆም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት ላይ ሲሆን የዚህ ሕገ-ወጥነት ተዋንያን የሆኑ አካላት ግን ከወዲሁ ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ አሳስቧል።

በአሀኑ ወቅት ለተከሰተው የኑሮ ውድነት አንደኛው መንሥኤ የግብይት ሥርዓቱ የተራዘመ መሆኑ እንደሆነ የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር ገልጿል።

ይህም አምራቾች እና ሸማቾችን ሳይሆኑ በግብይት ሂደቱ ውስጥ ምንም እሴት የማይጨምሩ አካላትን ብቻ ተጠቃሚ የሚሆኑበት አግባብ በመሆኑ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ መንሥኤ መሆኑን አስታውቋል።