መስከረም 14/2015 (ዋልታ) ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተበረከተላቸውን የክብር ዶክትሬት በዛሬ እለት በአካል ተገኝተው ተቀብለዋል።
ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ አሸባሪው ሕወሓት ሰሜን ወሎን በወረራ ይዞ በነበረበት ወቅት ለተራቡት አብልተዋል፣ ለተጠሙት አጠጥተዋል፣ ለታረዙት አልብሰዋል፤ ያዘኑትን አጽናንተዋል።
ለ5 ወራት በቆየው ወረራ የወልድያና አካባቢውን ሕዝብ ሃይማኖት፣ ዘር፣ ቋንቋ ሳይመርጡ ክፉ ቀንን አሳልፈዋል።
በዚህም ወላዶች፣ ቁስለኞች፣ በችግር ላይ የነበሩ ወገኖች ከጉዳት ተርፈው መልካም ቀንን እንዲያዩ አድርገዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፍሬው ተገኘ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው “ብዙዎች ከአካባቢያቸው በሚሸሹበት ወቅት በጦርነት ውስጥ ወደ ሚገኘው ሕዝባቸው በመሄድ የመከራ ቀን እንዲያልፍ ታሪክ የማይረሳው ሥራን ሠርተዋል” ብለዋል።
የከበረ ሥራን አከናውነው የከበሩትን በማክበራችን እኛም ብዙ አትርፈናል ነው ያሉት።
ልጇ ክብር በማግኘቱ ቤተክርስቲያን ደስ ብሏታል ያሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው።
ከዲቁና እስከ ሊቀ ጵጵስና ድረስ በትክክል የበጎች እረኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ሲሉም ምስክርነታቸውን መስጠታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ለ5 ወራት እህል፣ ውኃ፣ ልብስ፣ መብራት በሌለበት ወቅት ችግር ላይ ወድቆ የነበረን ሕዝብ በእግዚአብሔር ድጋፍ ወደ ሰላም እንዲመለስ ማድረጋቸውን ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ተናግረዋል።
“ሁሉ ከእርሱ፣ ሁሉ በእርሱ፣ ሁሉም ለእርሱ” በመሆኑ የመከራው ቀን አልፏል ነው ያሉት ብፁዕነታቸው።
“የተሰጠኝ ክብር ዶክትሬት ወገኑን ለማትረፍ መልካም ነገርን ሁሉ ላደረገ ሕዝብ ነው” ብለዋል።
ባለፈው ነሐሴ 21 ቀን 2014 ዓ.ም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለብፁዕ አቡነ ኤርምያስና ለኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የክብር ዶክትሬት መስጠቱ ይታወሳል።
በወቅቱ ለሐዋርያዊ ተልዕኮ ከሀገር ውጪ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በተወካያቸው በኩል የክብር ዶክትሬታቸውን ተቀብለው ነበር።