ተቋሙ በአፋር ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች የ5 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ

ጥር 21/ 2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አሸባሪው ሕወሓት በአፋር ክልል በፈፀመው ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል የ5 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሙላት ገዛኸኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጦርነቱ የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን ከመጠገን ጎን ለጎን የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች በጦርነቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት 2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የዓይነት እንዲሁም 3 ሚሊየን ብር የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።
ተቋሙ ሠራተኞቹን በማስተባበር ያደረገው የዓይነት ድጋፍ የህፃናት አልሚ ምግብ፣ መኮረኒ፣ ዱቄት፣ አልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን ያካተተ ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን በፍጥነት በመጠገን ከአፋር ሕዝብ ጎን መቆሙን በተግባር በማሳየቱ አመስግነዋል።
በክልሉ በዞን ሁለት አምስት ወረዳዎች ብቻ ከ300 ሺሕ ሰዎች በላይ ተፈናቅለው እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ነው ኃላፊው ያመለከቱት።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቀደም ሲል በአማራ ክልል በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች 7 ሚሊየን ብር የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ከኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡