ተተኳሽ ጥይቶችን ለፀረ ሰላም ኃይሎች ደብቆ ለማሳለፍ የሞከረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

መጋቢት 26/2014 (ዋልታ) ፖሊስ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ተተኳሽ ጥይቶችን በህገ ወጥ መንገድ በጭነት ተሽከርካሪ ላይ ደብቆ ለማሳለፍ የሞከረው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ።

ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር የዋለው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 -6189 አ.አ በሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ 404 ተተኳሽ ጥይቶችን በዱቄት ከረጢት ውስጥ ደብቆ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ዲሬ ጉዶ ከተማ ማዞሪያው አካባቢ እንደደረሰ መሆኑን የወረዳው ፖሊስ ኃላፊ ኮማንደር ቶሎሳ መልካ ገልጸዋል።

ተተኳሽ ጥይቶቹ ለፀረ ሰላም ኃይሎች ለማስተላለፍ እንደሆነ መጠርጠሩን ያመለከቱት ኮማንደር ቶሎሳ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባደረገው ክትትል በቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰብ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመግታት የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ያሉት ኮማንደር ቶሎሳ ኅብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመተባበር ወንጀልን እንዲከላከል ጠይቀዋል፡፡

በወረዳው በተያዘው ወር ብቻ የአሁኑን ሳይጨምር 862 ተተኳሽ ጥይቶች መያዛቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW