ቱሉዲምቱ አካባቢ በደረሰውን የእሳት አደጋ የ1 ሰው ህይወት ስያልፍ በ5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉ ተገለጸ

መስከረም 14/2015 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቱሉዲምቱ አካባቢ ትላንት ሌሊት በአነስተኛ የንግድ ሱቆች ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ከአደጋው ማዳን መቻሉን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ ንጋቱ ማሞ ለኢዜአ እንዳሉት አደጋው የደረሰው ሌሊት 7 ሰአት ከ44 ደቂቃ ሲሆን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ቱሉዲምቱ አካባቢ ነው።

በአካባቢው የደረሰውን የእሳት አደጋ በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ በመቆጣጠር ከፍተኛ ግምት ያለው ንብረት ከአደጋው ማዳን ተችሏል ብለዋል።

በአደጋው አነስተኛ የንግድ አገልግሎት የሚሰጡና 15 የሚሆኑ በላስቲክ፣ በሸራና በአነስተኛ ቁሳቁስ የተሰሩ መጠለያዎች እንደተጎዱ አንስተው የእሳት አደጋው ወደሌላ ስፍራ ሳይዛመት በአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በቀላሉ መቆጣጠር መቻሉን ገልፀዋል።

በዚህ ሂደትም አምስት ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ከአደጋው ማዳን እንደተቻለ ጠቁመው ይሁን አንጂ ከነዚህ ሱቆች መካከል በመጻሕፍት ንግድ ላይ የሚሰራ እድሜው 32 ዓመት የሆነ ሰው በሱቁ ውስጥ እንደተኛ ህይወቱ ያለፈ መሆኑን ተናግረዋል።

በደረሰው የእሳት አደጋ 300 ሺሕ ብር የሚገመት ንብረትም መውደሙንም አመልክተዋል።

የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር ከአቃቂ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሁለት የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪ እና አንድ አንቡላንስ እንዲሁም 15 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች መሰማራታቸው ተጠቅሷል።

የአደጋው መንስኤ በፖሊስ እየተጣራ ስለመሆኑም በመረጃው ተመልክቷል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW