ቱርክ ከሶሪያ ጋር በሚያዋስናት የድንበር አካባቢ ወታደራዊ ዘመቻ ልትጀምር ነው

ግንቦት 16/2014 (ዋልታ) ቱርክ ከሶሪያ ጋር በሚያዋስናት የድንበር አካባቢ አዲስ ወታደራዊ ዘመቻ ልታከናውን መሆኑን ፕሬዝዳን ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አስታወቁ፡፡

አንካራ ይህንን ወታደራዊ ዘመቻ ለማድረግ ያቀደችው በቱርክ ቁጥጥር ስር ባሉ ሁለት የቀጣናው አካባቢዎች አዲስ ግጭት ይፈጠራል የሚል ስጋት ስላደረባት መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ትላንት የካቢኔ ስብሰባ ካካሄዱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ቱርክ ከሶሪያ ጋር በምትጋራው ድንበር 30 ኪሎ ሜትሮች ድረስ ዘልቃ በመግባት የአካባቢውን ሰላም አስተማማኝ ማድረግ እንደምትፈልግ ጠቁመዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በዚህ መግለጫቸው ዝርዝር ጉዳዮችን ከማብራራት የተቆጠቡ ሲሆን፤ የሃገሪቱ የደህንነት አካላት እና ጦሯ ዝግጅታቸውን ሲያጠናቅቁ ቀጣናውን ከስጋት ነጻ ለማድረግ የጀመረችውን ኦፕሬሽን ታጠናቅቃለች ብለዋል፡፡

ቱርክ ወታደራዊ ዘመቻ ለማድረግ ያቀደችበት ስፍራ በሶሪያ ዴሞክራቲክ ሃይል እና በኩርድ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የሚገኝ መሆኑን የአልጀዚራ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በነስረዲን ኑሩ