ታሪክን ተምሮ የራስን አሻራ ለማሳረፍ ወታደራዊ ቅርሶች ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑ ተጠቆመ

ታኅሣሥ 7/2015 (ዋልታ) ፊት አውራሪ ሀብተ ጊዎርጊስ ዲኔግዴ እና ሜጀር ጄነራል ግዛው በላይነህ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ወታደራዊ ቁሳቁስ ለመከላከያ ቅርስ ጥበቃና ሙዚየም ገቢ ሆነዋል።

ፊት አውራሪ ሀብተ ጊዎርጊስ ዲነግዴ ከ1900 እስከ 1919 ዓ.ም የጦር ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን በጦር ሜዳ ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን ቁሳቁስ ገቢ ያደረጉት ሐኪም አበበች ሽፈራው ናቸው።

ዘጠነኛው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም የሆኑት ሜጄር ጀኔራል ግዛው በላይነህ በውትድርና አመራርነታቸው ሲገለገሉባቸው የነበሩ ቁሳቁስን እና ሌሎች ማስተወሻዎችን ልጃቸው ግሩም በላይነህ ገቢ አድርገዋል።

በቅርሶቹ ርክክብ ላይ የተገኙት በመከላከያ ሚኒስትር ልዩ ስታፎች ጉዳይ ዘርፍ ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል ጥሩዬ አሰፌ የሠራዊቱን ቅርስ በመሰብሰብ ለትውልዱ እንዲተላለፍ ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ትውልዱም ከአባቶቻችን ታሪክ ተምሮ የራሱን አሻራ እንዲያስቀምጥ እና እንዲማርበት ወታደራዊ ቅርሶች ዕድል ይፈጥራሉ ሲሉም ተናግረዋል።

ለመከላከያ ቅርስ ጥበቃ እና ሙዚየም ወታደራዊ ቅርሶችን በመስጠት የሀገር እና የህዝብ ሀብት እንዲሆኑ ላደረጉ ግለሰቦችም  ሜጄር ጄኔራል ጥሩዬ ምስጋና አቅርበዋል።

የመከላከያ ቅርስ ጥበቃ እና ሙዚየም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል አብዱልቃድር ደበሹ በበኩላቸው የሰራዊቱን ታሪክ እና ቅርስ በመሰብሰብ ለትውልድ እንዲተላለፍ እየተሠራ ያለው ስራ ትውልዱ በተለይ ታሪካዊውን የኢትዮጵያዊያንን ጀግንነት በሚገባ እንዲገነዘቡ ያግዛል ብለዋል።

በመርኃ ግብሩ ላይ የተገኘው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ታሪክን መሠብሠብ ጀግኖችን እንዲሁም የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል በመሆኑ ትውልዱ ወደ ሙዚየም የገቡ ቅርሶችን ተመልክቶ የራሱን አሻራ እንዲያስቀምጥ እና የተሻለ ነገር እንዲሰራ ያነሳሳል ብሏል።

የአበበ ቢቂላ እና የማሞ ወልዴ ታሪክ እንዳመጣኝ ሁሉ ሁሉም ሰው በየቤቱ ያለውን ወታደራዊ ቅርስ ለመከላከያ በመስጠት የሀገራችንን ታሪክ ማስቀጠል አለብን ሲልም አክሏል።

በዕለቱም ወታደራዊ ቅርሱን ላስረከቡ ለሐኪም አበበች ሽፈራው እና ለሜጀር ጄነራል ግዛው በላይነህ ልጅ ግሩም በላይነህ የምስክር ወረቀት እንደተበረከተላቸው ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።