ትሕነግ በቆቦ እና ጭና አሰቃቂ የጦር ወንጀሎች መፈፀሙን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለፀ

የካቲት 9/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ትሕነግ ቆቦ እና ጭናን ተቆጣጥሮ በቆየባቸው ጊዜያት ከፍተኛ የጦር ወንጀሎች መፈፀሙን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት አረጋግጧል፡፡

የሽብር ቡድኑ በሐምሌ እና ነሐሴ ወራት በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ደርሶበት የነበረውን ሽንፈት ለመበቀል መሳርያ ያልታጠቁ በርካታ ዜጎችን መግደሉን እና ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት ጀምሮ ያሉ ሴቶችንም በጅምላ መድፈሩን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

አምነስቲ ያነጋገራቸው የዓይን እማኞች በርካታ የቆቦ ነዋሪዎች በቡድኑ በግፍ መገደላቸውን ሲመሰክሩ አምነስቲ የሳተላይት ምስልን ተጠቅሞ በመረመራቸው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ቅዱስ ሚካኤል አብያተ ክርስቲያናትም እነዚህን ግድያዎች የሚያመላክቱ አዳዲስ መቃብሮች ማግኘቱን ጠቁሟል፡፡

በጭናም እንዲሁ የሽብር ቡድኑ በርካታ ታዳጊ ሴቶች እና እናቶችን በጅምላ አስገድዶ መድፈሩን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በልጆቻቸው ፊት ጭምር በሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በጅምላ መደፈራቸውን እና ነገሩ በሚፈፀምበት ወቅትም ድብደባ፣ የግድያ ዛቻ እና ዘር ተኮር ዘለፋ ያደርሱባቸው እንደነበር አምነስቲ ያነጋገራቸው የጥቃቱ ሰለባዎች ገልፀዋል፡፡

የጥቃቱ ሰለባዎች በደረሰባቸው ከፍተኛ አካላዊ ጉዳት ሳቢያ ለወራት በሆስፒታል እንዲቆዩ መገደዳቸውን የአምነስቲ ሪፖርት ጠቅሷል፡፡

የሽብር ቡድኑ ከነዚህ አሰቃቂ የጦር ወንጀሎች በተጨማሪ በሁለቱም አካባቢዎች የነዋሪዎችን ቤቶች ንብረት መዝረፉን እና የህዝብ መገልገያ ተቋማትንም ማውደሙን አምነስቲ በሪፖርቱ አስቀምጧል፡፡

የጤና ተቋማት ከተዘረፉት የህዝብ መገልገያዎች መካከል በመሆናቸው የአስገድዶ መደፈሩ ሰለባ የሆኑት ነዋሪዎች ሕክምና እንዳያገኙ አሊያም ሕክምናውን በሌሎች ከተሞች ለማግኘት ለሳምንታት ያለ ጤና እርዳታ እንዲቆዩ ማድረጉ ተገልጿል፡፡