ትምህርታቸውን በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ሲከታተሉ የነበሩ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተመረቁ

መጋቢት 28/2014 (ዋልታ) በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተመረቁ።
ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 271 የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነው ያስመረቀው።
የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ሀብታሙ አበበ (ዶ/ር) “ዛሬ የምትመረቁ ተማሪዎች ስለሰላም አስፈላጊነት ከናንተ በላይ ምስክር የለምና በምትሄዱበት ሁሉ የሰላም አምባሳደር ሁኑ” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በአጠቃላይ ከተመረቁት 271 ተማሪዎች 110 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በትግራይ ክልል በነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታችሁን ሲትከታተሉ የነበሩ ተማሪዎች በጦርነቱ ምክንያት ትምህርታችሁን መቀጠል ባለመቻላቸው በሌሎች የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ዮሴፍ ታደሰ (ከዎሳእና)