ትብብር እና አንድነታችን የድል ብስራታችን መሰረት ነው – ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ

ሐምሌ 21/2014 (ዋልታ) ትብብር እና አንድነታችን የድል ብስራታችን መሰረት ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በአትሌቲክስ ቡድኑ የተገኘውን ዉጤት በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ኢትዮጵያን ያስቀደሙ ድንቅ አትሌቶቻችን በ18ኛው የኦሪገን ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመላ ኢትዮጵያውያን ክብር፣ ኩራት፤ ደስታን አብስረዋል ብለዋል በመልዕክታቸው።

ሀገራቸውን በዓለም መድረክ አስጠርተው በአሸናፊነትና በድል ተመልሰዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ኢትዮጵያዊነት የድል አድራጊነት ተምሳሌት፣ አልበገርም ባይነትና የአሸናፊነት ወኔም ነው ብለዋል።

የአትሌቶቻችን አሸናፊነት እና ድል አድራጊነትም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ነው ሲሉም አክለዋል።

ለሀገራቸው ኢትዮጵያ ክብር ተሰልፈው በዓለም አደባባይ ስሟንና ሰንደቋን ከፍ አድርገው፣ በድል ለተመለሱ ድንቅ አትሌቶቻችንና መላ ኢትዮጵያውያን በሙሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡