ትውልደ ኢትዮጵያዊው ኦባላ አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ የፈፀመውን ግፍና ጭፍጨፋ ለባይደን አስረድቻለሁ  አለ

ኅዳር 23/2014 (ዋልታ) ትውልደ ኢትዮጵያዊው ኦባላ ኦባላ አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ የፈፀመውን ግፍ እና በዜጎች ለይ በማድረስ ላይ ያለውን  ጭፍጨፋ ለአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስረድቻለሁ አለ።

በጋምቤላ ክልል የተወለደውና በአሜሪካ ሚኔሶታ ኦስቲን የምክር ቤት አባል የሆነው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ኦባላ ኦባላ ፕሬዝዳንት ባይደን በመሰረተ ልማት ጉዳዮች ዙሪያ በነበረ  ስብሰባ ላይ ንግግር አድርገው ሲወጡ በአካል አግኝቶ እንዳናገራቸው በግል የማህበራዊ ትስስር ገፁ ባሰፈረው ፅሑፍ ገልጿል።

ኦባላ ከፕሬዝዳንት ባይደን ጋር በነበረው ቆይታ በግሉ በተወለደበት ጋምቤላ ከዚህ ቀደም በአሸባሪው ህወሃት ከተጠነሰሰ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ተርፎ መውጣቱን እንደገለጸላቸውም ጠቁሟል።

ኦባላ ፕሬዝዳንቱን ያገኘበትን አጋጣሚ በመጠቀምም ትውልድ ሀገሩ ኢትዮጵያ በአሸባሪው የሕወሓት አገዛዝ የደረሰባትን ግፍ እና መከራ እንዲሁም በአሁን ሰዓት አሸባሪ ቡድኑ እያደረሰ ባለው ትንኮሳ እና ግጭት ከፍተኛ ችግር መጋረጡን፤ በዚህም ሳቢያ ንፁሃን  ዜጎችን ለከፋ ችግር መዳረጉን አብራርቶላቸዋል።

አሸባሪ ቡዱኑ መንግስታዊ ስልጣን ይዞ ኢትዮጵያን ባስተዳደረበት ባለፉት 27 ዓመታት በተወለደበት ክልል የአኝዋክ ጎሳ ላይ ያደረሰውን ጭፍጨፋ እና በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰባቸውን ሰቆቃ በተመለከተም ማስረዳቱንም  አብራርቷል።

ይህንን በመረዳታቸው ፕሬዝዳንት ባይደን የተሰማቸውን ሃዘን እንደገለጹለትም በጽሁፉ አስፍሯል።

ትውልደ ኢትዮጵያዊው ኦባላ አሜሪካ ሽብርተኛውን የሕወሓት ጁንታ ቡድን መደገፍ እንደሌለባት ማብራራቱንም ጠቁሟል።

“በአሜሪካ  በስልጣን ላይ ያለ ፕሬዝዳንት ሆኖ  ስለ ህዝቤ እና ስቃያቸው ሲሰሙ ይህ የመጀመሪያው ነው” ያለው ኦባላ ታሪኬን እና በአሜሪካ ሚኒሶታ  በኦስቲን ኤም ኤን የማደርገውን ስራ ለማካፈል  በቅርቡ  ነጩን ቤተመንግስት  ለመጎብኘት ዝግጅት አደርጋለሁም ብሏል።