ትውልዱ ጊዜው የሚጠይቀውን የአርበኝነት ሥራ በመስራት የራሱን ታሪካዊ ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል

ሚያዝያ 27/2014 (ዋልታ) የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሁኑ ትውልድ ጊዜው የሚጠይቀውን የአርበኝነት ሥራ በመስራት የራሱን ታሪካዊ ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አሳሰበ።

ምክር ቤቱ 81ኛው የአርበኞች ቀን መታሰቢያ በዓል አስመልክቶ ያስተላለፈው መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-

እንኳን ለ81ኛው ዓመት የድል ቀን አደረሳችሁ ! አደረሰን!

የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር  ቤት

ፋሽስት ጣሊያን   ኢትዮጵያን የቀኝ ግዛቱ  ለማድረግ   በ1888 በሰሜን ኢትዮጵያን  ድንበር ጥሶ  ወረራ አካሂዷል።

ይህን ተከትሎም ጀግኖች  ቅድመ አያቶቻችን   ከዳር  ዳር   ተጠራርተው ወደ  ሰሜን በመትመም ለአገር ክብርና ጥቅም ሲሉ  በአንድነት  ተዋድቀዋል፤ አጥንት ደማቸውን ከስክሰው ና አፍሰው በከፈሉት የሕይወት  መስዋእትነት  አንድነቷ የጠበቀ ነፃ  ሉዓላዊ አገር  አስረክበውናል ። በአንድ ቀን የጦር ሜዳ ዉሎ   ጀግኖች  አባቶቻችን  ባደረጉት የአርበኝነት ተጋድሎ የጣልያንን ተስፋፊና ወራሪ ኃይል  አድዋ ላይ ድል አድርገው፤ አይቀጡ ቅጣት ቀጠው አሳፍረው  መልሰውታል።

አድዋ ላይ  ሽንፈት ያጋጠመው ፋሽስት ጣሊያን ከ40 ዓመት    በኋላ  ዳግም  ኢትዮጵያን ለመውረር  ተዘገጀ። የምዕራቡ ዓለም ከደረሰበት የሳይንስና ቴክኖሎጂ  ዕድገት  የተፈበረኩ  ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን  እስከ አፍንጫው የታጠቆና  እጅግ የሰለጠነ  ዘመናዊ ጦር ይዞ  መጣ ፤በዓለም አቀፍ ሕግ ደረጃ የተከለከረውን  የመርዝ ጋዝ በመጠቀም ጭምር  በ1928 ዓ.ም አጋራችንን ዳግም ሊወር ችሏል።

ፋሽት ጣሊያን ኢትዮጵያን  ደግም ለመውረር  የመጣው ለኢትዮጵያና ሕዝቧቿ ጥቅም አልነበረም፤ ይልቁንም  በአድዋ ጦርነት  የደረሰበትን ሽንፈትና አሳፋሪ ጠባሳ ለመሰረዝ ፤ ኢትዮጵያን ለመበቀልና ህዝቿን ለማዋረድ ነበር።

አልተሳካለትም እንጂ !

ፋሽት ጣሊያን በአምስት ዓመት ቆይታው  በየካቲት 12  19 29 ዓ.ም  ያካሄደውን አረመናዊ   ጭፍጨፋን ጨምሮ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ አሰቃቂ ግፍና በደል ፈፅሟል።

ኢትዮጵያውያንን ለማበርከክና ነፃነታቸውን ለመንጠቅ  የሚችለውን ሁሉ ቢያደርግም  እንዳሰበው አልሆነም  ።

በየአከባቢው ያሉ ኢትዮጵያውያን እናት አባት  አርበኞች  ነፍጥ አንግበው ፤ ጎራዴ ስለው ፤ ዱር ቤቴ ብለው  በዱር በገደሉ ረሃብና ቸነፈር  ሳይበግራቸው  ፈሽስት ጣሊያንን መግቢያና መውጫ አሳጥተው ታግለውታል። በአርበኝነት  ተዋድቀው ጠላትን  ከአገር አባረው ለድል ቀን በቅተዋል፤  ከ5 ዓመት የአርበኝነት ትግል በኋላም  አዲስ አበባን በመግባት  የኢትዮጵያን ሰንቅ ዓላማ   በዛሬዋ ዕለት  ሚያዚያ 27ቀን 1933 ዓ.ም ሊሰቀሉ ችለዋል።

አገር በየጊዜው በሚፈጠሩ  ጀግኖቿና አርበኞች ልጆቿ አንድነቷ ፀንቶ፣ ነፃነቷ ተጠብቆና ዳር ድንበሯ ተከብሮ በትውልድ ቅብብሎሽ እነሆ ከዚህ ደርሳለች።

የአሁኑ ትውልድም ጊዜው የሚጠይቀውን የአርበኝነት ስራ በመስራት  የራሱን ታሪካዊ ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል።

የእናት አባቶቹ ታሪክ ወራሽ  ትውልድ ብቻ ሳይሆን የራሱን ታሪክ በመስራት አገራችን ኢትዮጵያ የበለፀገች፣ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባትና እውነተኛ ዴሞክራሲ የሚተገበርባት አገር  እንድትሆን  ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት የስራ መስክ ሁሉ ለአገር ክብርና ጥቅም   የልማት አርበኛ  ሊሆን ይገባል።

እናቶቻችንና አባቶቻችን ጊዜው የሚጠይቀውን የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር  ነፃነቷና አንድነቷ

የተጠበቀ አገር አውርሰውናል።  እኛም ዘመኑ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት በመክፈል  ከድህነት የወጣች የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትዉልድ ለማስረከብ  ተግተን መስራት ይኖርብናል።

ዘላለማዊ  ክብር ለእናት አባት አርበኞች!

እንኳን አደርሳችሁ ! አደረሰን!

መልካም የድል ቀን!

የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ሚያዝያ 27 ቀን 2014 ዓ.ም