ቻይና ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አዲስ ልዩ መልዕክተኛ ሾመች

የካቲት 15/2014 (ዋልታ) ቻይና ዡዪ ቢንግን የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናን በቅርበት የሚከታተል ልዩ መልዕክተኛ አድርጋ መሾሟን አስታወቀች፡፡

ቻይና ልዩ ልዑኩን በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ እንዲሰሩ ምደባ የሰጠችበት ዋናው ምክንያትም በአካባቢው እየተስተዋሉ ላሉ ችግሮች መፍትሔ እንዲያፈላልጉ በማሰብ መሆኑ ታውቋል፡፡

ዡዪ ቢንግ ለቀጣናው አዲስ የተሾሙት ዲፕሎማት ሲሆኑ በአፍሪካ፣ በአሜሪካ እና አውስትራሊያ የዲፕሎማሲ ዘርፍ ላይ የካበተ ልምድ ያላቸውና ቀደም ሲልም በፓፑዋ ኒው ጊኒ የቻይና አምባሰደር ሆነው ስለመሥራታችው የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡

ልዩ መልዕክተኛው በአገራቱ በሚኖራቸው ቆይታ የቻይናን ሰላማዊ ልማት ዕቅድ በማስተዋወቅ የቀጣናው አገራት ከዕቅዱ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን እና ዘላቂ መረጋጋት፣ ልማት እና ብልጽግና እንዲያረጋግጡ ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ተልዕኮ እንደተሰጣቸው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን በዕለታዊ መግለጫቸው ተናግረዋል፡፡

ይህ ሹመት በተያዘው ዕቅድ መሰረት የተከናወነ መሆኑን ያስታወሰው ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ቻይና በቀጣናው ማስጠበቅ የምትፈልገው ብሔራዊ ጥቅም በጅቡቲ የጦር ሰፈር /ቤዝ/ መገንባት እና ቁልፍ ዓለም ዐቀፍ የመርከብ ማመላለሻ መስመር ላይም የቅርብ ክትትል ማድረግን እንደሚያካትት ተገልጿል፡፡

ቻይና ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና አዲስ ልዩ መልዕክተኛ እንደምትሾም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጥር ወር ላይ በምስራቅ አፍሪካ አገራት ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት መግለጻቸውን አስታውሶ ኢዜአ ዘግቧል፡፡