ቻይና ምንጊዜም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በጽናት ትቆማለች – በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር

ታኅሣሥ 23/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ሁኔታ ምንም ያህል ቢቀየር ቻይና ምንጊዜም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በጽናት ትቆማለች ሲሉ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዛዎ ዝሂዩን ገለጹ፡፡

አምባሳደሩ የፈረንጆቹን የ2022 አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት የተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት የቻይና-ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋርነት በጥልቀትም ሆነ በስፋት እያደገ የሄደበት መሆኑን ገልጸው የአገራቱ ትብብር ለቻይና-አፍሪካ ግንኙነት ተምሳሌት ሆኖ እንደቀጠለ ጠቅሰዋል።

እንደ ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ የትብብር አጋሮች የኢትዮጵያ ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ሁኔታ ምንም ያህል ቢቀየር ቻይና ምንጊዜም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በጽናት እንደምትቆም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

የፈረንጆቹ አዲሱ ዓመት ለቻይና-ኢትዮጵያ ወዳጅነትና ትብብር ትልቅ እድሎችን ይዞ እንደሚመጣ ያላቸውን እምነት የገለጹት በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር የሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በጋራ እንደሚሰሩም መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከኢምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡