ችግረኛ ዜጎችን ለመርዳት ቢጥርም ከአቅሙ በላይ እንደሆነበት የአማራ ክልል መንግሥት አስታወቀ

ጥቅምት 28/2014 (ዋልታ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ከዓለም የምግብ መርሀ ግብር ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያዩ።
አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በያዛቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ንፁሃንን ከመግደል እስከ ማፈናቀል የደረሱ ግፎችን እየፈፀመ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ አንስተዋል።
የክልሉ መንግሥት በአሸባሪ ቡድን ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ዜጎችን ለመርዳት ጥረት እያደረገ ቢሆንም ባለው የአቅም ውስንነት ምክንያት ችግሩን ማቃለል አለመቻሉን ገልፀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ድጋፍ አቅራቢ ተቋማት እስካሁን ችግሩን ለማቃለል ላደረጉት ርብርብ ምስጋና ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ አሁንም በአሸባሪ ቡድኑ ሕወሓት ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ አፋጣኝ ድጋፍ በማድረግ ችግሩን ለማቃለል እገዛ እንዲደረግ ጠይቀዋል።
እንደኢቢኮ ዘገባ በአሁኑ ወቅት በአሸባሪ ቡድኑ ወረራ ምክንያት 7 ሚሊዮን የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች አደጋ ላይ መውደቃቸውንና ከዚህ ውስጥ 6 ሚሊዮን የሚሆኑት አስቸኳይ ሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ናቸው ተብሏል፡፡