“ችግኝ እየተከልን ሃገራችንን እንጠብቃለን” በሚል የካምባታ ጣምባሮ ዞን የወጣት አደረጃጀቶች በኮይሻ ፕሮጀክት “ሀላላ” ክላስተር ችግኝ ተከሉ

ነሃሴ 08/2013 (ዋልታ) – “ችግኝ እየተከልን ሃገራችንን እንጠብቃለን” በሚል መሪህ በዳውሮ ዞን የገበታ ለሃገር ኮይሻ ፕሮጀክት ሃላላ ክላስተር የተገኙት የካምባታ ጣምባሮ ዞን በጎ አድራጎት ወጣቶች በታሪካዊ ሥፍራዉ የችግኝ ተከላ አከናዉነዋል።
በጎ አድራጎት ወጣቶች ከካንባታ ጣምባሮ ዞን ወደ ዳውሮ ዞን የመጡት በገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት ሀላላ ክላስተር ችግኝ በመትከልና ደም በመለገስ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን መቆማቸውን በተግባር ለማሳየት መሆኑን ገልፀዋል።
የካምባታ ጣምባሮ ዞን የወጣቶች አደረጃጀቶችን እንኳን ወደ ለምለምቷ ዳውሮ ዞን በሰላም መጣችሁ ያሉት የዳውሮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ባንጉ እንደዚህ አይነት ግኑኝነቶች በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።

በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ሀላላ ክላስተር ላይ ችግኝ በመትከልና ደም በመለገስ በሀገራችን የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠልና የአሸባሪውን ህወሃት ሴራ በመቃወም ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መሆናቸውን ለማሣየት እንደመጡ የካምባታ ጣምባሮ ዞን ወጣቶች አስተባባሪ ወጣት ሄኖክ ታደሴ ገልፀዋል።
ወጣቶቹ ችግኝ ከመትከል ጎን ለጎን የታላቁን የንጉስ “ሀላላ” የመከላካያ የድንጋይ ካብና በገበታ ለሀገር ኮይሻ ፕሮጀክት የሀላላ ክላስተር የግንባታ ሂዴትንም ጎብኝተዋል።
ለወጣቶች የዞንና የወረዳ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችና የአከባቢው ህብረተሰብ ደማቅ አቀባበል ማድረጋቸውን የዳውሮ ዞን መን/ኮ/ጉ/መምሪያ መረጃ ያመለክታል።