ኃያሉ ፈጣሪ ብቻ ነው ከውድድሩ እንድወጣ ሊያሳምነኝ የሚችለው – ጆ ባይደን

ጆ ባይደን

ለሁለተኛ ዙር የአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ዕጩ ሆነው የቀረቡት ጆ ባይደን ከአንዳንድ የፓርቲያቸው አመራሮች እና ደጋፊዎቻቸው ዘንድ በዕድሜያቸው መግፋት ምክንያት ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

የ81 ዓመቱ አዛውንት ራሳቸውን ከዴሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩነት እንዲያገሉና በምትካቸው ትራምፕን ለመገዳደር የሚችል ዕጩ እንዲቀርብ ነው ጥሪ እያቀረቡ ያሉት።

ባይደን ባለፈው ሳምንት ከሪፐብሊካኑ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር ክርክር እርጅናው እንደተጫጫናቸውና ለመጭው 4 ዓመታት አሜሪካን ለመምራት የሚያስችል ቁመና ላይ ስለመሆናቸው በፓርቲያቸው አመራሮችና ደጋፊዎቻቸው ዘንድ ጥርጣሬ ፈጥሯል።

በክርክሩ ወቅት በንግግሮቻቸው መደነቃፍ፣ የሀሳብ መዛነፍ፣ የጀመሯቸውን አረፍተነገሮች ለመጨረስ ሲሳናቸው እንዲሁም የሚጣረሱ ነገሮችን ሲናገሩ ተስተውለዋል።

በክርክሩ የሪፐብሊካኑ እጩና የቀድሞው ፕሬዝዳንት በብዙ ረገድ ጠንክረውና ከዚህ በፊት ከሚታወቁበት ስሜታዊነት ሰከን ብለው የቀረቡበት ነበር።

በዚህም ክርክሩ ዶናልድ ትራምፕ እንዳሸነፉና ባይደን የሀሳብ የበላይነት እንደተወሰደባቸው የሚዲያዎች፣ የፓርቲው አመራርና ደጋፊዎች መወያያ ሆነው ሰንብተዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን በምርጫ ክርክሩ ወቅት ላጋጠማቸው ደካማ አጀማመር ጉንፋንና ድካምን እንደ ምክንያት ያቀረቡ ሲሆን ሰሞኑን ከፍተኛ የገፅታ ግንባታ ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ።

የ81 ዓመቱ አዛውንት ጆ ባይደን ከኤቢሲ ኒውስ ጋር በነበራቸው የ22 ደቂቃ ቆይታም “በየቀኑ የአዕምሮ ንቃት ምርመራ (cognitive test) አደርጋለሁ፤ ከእኔ የተሻለ ለፕሬዝዳንትነት ብቁ የሆነ ሰው አለ ብዬ አላምንም” ብለዋል።

“በጣም አርጅቷል የሚሉ በርካታ ንግግሮችን እሰማለሁ፤ ለ15 ሚሊዮን ሰዎች ሥራ ለመፍጠር በጣም አርጅቻለሁ? ለ5 ሚሊዮን ተማሪዎች የኮሌጅ ዕዳን ለመሰረዝ በጣም አርጅቻለሁ? ዶናልድ ትራምፕን ለማሸነፍ በጣም ያረጀሁ ይመስላችኋል?” በማለት በተወዳዳሪነታቸው እንደሚቀጥሉ በአንድ የምረጡኝ ቅስቀሳ ንግግራቸው አስረግጠዋል።

“ምላሼን ልንገራችሁ፣ እወዳደራለሁ ድጋሚም አሸንፋለሁ” አሉ ጆ ባይደን በመድረኩ ለተሰበሰቡት ሰዎች ምንም እንኳ በተሰበሰበ የህዝብ አስተያዬት ከ70 በመቶ በላይ የፓርቲ ደጋፊዎች ሰውዬው ብቁ አይደሉም ቢሉም።

ይህን ተከትሎ አንዳንድ ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች ጆ ባይደን በሌላ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ መተካት እንዳለባቸው በግልፅ ጥሪ እያቀረቡ ነው።

ምክትል ፕሬዝዳንታቸው ካማላ ሃሪስ ለጆ ባይደን ዕጩነት ድጋፍ እየሰጡ ቢሆንም ብዙዎች በፕሬዝዳንት ባይደን ምትክ እሳቸው ቢወዳደሩ እንደሚፈልጉ ድምጾች እየተሰሙ ነው።

ከየአቅጣጫው የዕጩነት ቦታውን ይልቀቁ የሚል ጫና የበረታባቸው ጆ ባይደን ግን በአንገቴ ካራ ያሉ ይመስላሉ። ኃያሉ ፈጣሪ ብቻ ነው ከውድድሩ እንድወጣ ሊያሳምነኝ የሚችለው ሲሉም ነው ለኤቢሲ ጋዜጠኛ የመለሱለት።