ናይጄሪያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአየር መንገዷ የቴክኒክ አማካሪ እንዲሆን መረጠች

መስከረም 6/2015 (ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የናይጄሪያ ኤር የቴክኒክ አማካሪና ባለድርሻ እንዲሆን መመረጡ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቴክኒክ የሚያማክረው ናይጄሪያ የአየር መንገዷ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማሳደግ በብሔራዊ ደረጃ የያዘችው እቅድ ተግባራዊ መሆን በሚችልበት መንገድ ላይ ነው ተብሏል፡፡

ጉዳዩ የሚመለከታቸው የናይጄሪያ ባለስልጣናት የአማካሪነቱ ስራ ለማን ይሰጥ የሚለውን ለመወሰን ለወራት ያህል ጥናት ሲያደርጉ መቆየታቸውን የኦልአፍሪካ ዘገባ አመላክቷል፡፡

ከጥናቱ መጠናቀቅ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተመራጭ መሆኑን ተከትሎ ከሀገሪቱ የአቪየሽን ሚኒስቴር የተውጣጣ ቡድን ከአየር መንገዱ ጋር ለመነጋገር ዛሬ ወደ አዲስ አበባ ማቅናቱንም ዘገባው አክሏል፡፡

ሁለቱ አካላት በአዲስ አበባ ከተወያዩ በኋላ ስምምነት እንደሚፈራረሙ የተገለጸ ሲሆን ከስምምነት ፊርማው በኋላ የናይጄሪያ መንግስት ጉዳዩን በይፋ እንደሚገልጸው ዘገባው አስነብቧል፡፡
በነስረዲን ኑሩ

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW