“ናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት” የተሰኘ መርኃ ግብር ሊካሄድ ነው

ግንቦት 17/2014 (ዋልታ) “ናፍቆት የድሬዳዋ ሳምንት” የተሰኘ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች የሚያሳትፍ መርኃ ግብር እንደሚካሄድ ተገለጸ።

መርኃ ግብሩ ከሐምሌ 11 እስከ 16 ቀን 2014 ዓ.ም የሚከናወን ሲሆን ዝግጅቱን የድሬዳዋ አስተዳደርና ሁነቱን ለማስተባበር የተቋቋመው ኮሚቴ በጋራ እንደሚያዘጋጁት ተነግሯል።

የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ዝግጅቱ የድሬዳዋን ከተማ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴዎች የማጠናከርና የዳያስፖራውን ተሳትፎ የማሳደግ አላማ አለው ብለዋል።

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የከተማዋ ተወላጆችና ወዳጆች የድሬዳዋን ማኅበራዊ ችግሮች በሚያቃልሉ ሥራዎችና በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

የዳያስፖራዎቹን ተሳትፎ በተሻለ ሁኔታ ለማሳደግ መርኃ ግብሩ የራሱ አበርክቶ እንደሚኖረውና አስተዳደሩ ለዝግጅቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ዳያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቤል አሸብር በመርኃ ግብሩ የንግድና መዝናኛ ዝግጅቶች ጨምሮ የተለያዩ ሁነቶች ይከናወናሉ ብለዋል።

ከዝግጅቱ የሚገኘው ገቢ በአስተዳደሩ ለሚከናወኑ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ማስፈጸሚያ እንደሚውል ጠቁመዋል።

የመርኃ ግብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሳራ ሀሰን በበኩላቸው ለዝግጅቱ የሚያስፈልጉ ሥራዎች መጀመራቸውንና የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች በዝግጅቱ ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ኮሚቴው የመርኃ ግብሩ ዝግጅት እና ዳያስፖራው በድሬዳዋ ከተማ በልማትና ኢንቨስትመንት ሥራዎች ያለውን ተሳትፎ ማሳደግ ያስችላል የተባለ የመግባቢያ ሰነድ ከከተማው አስተዳደር ጋር መፈራረሙን ኢዜአ ዘግቧል።