ኔቶ ለሳይበር ጥቃቶች ወታደራዊ ምላሽን ሊጠቀም እንደሚችል አስታወቀ

ሰኔ 09/2013 (ዋልታ) – የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት “ኔቶ” ለሳይበር ጥቃቶች ወታደራዊ ምላሽን ሊጠቀም እንደሚችል አስታወቀ፡፡

ትናንት በብራስልስ በተካሄደው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት ስብሰባ ላይ አባላቱ የተሟላ የሳይበር መከላከያ ፖሊሲን ባጸደቁበት ወቅት ነው ይህን ሃሳባቸውን ያሳወቁት፡፡

የሳይበር ምህዳሩ “ውስብስብ ፣ አደገኛ ፣ አስቸጋሪ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ነው” ሲል ኔቶ በመግልጫዉ አትቷል።

የቅርብ ጊዜውን ራንሰምዌር ጥቃትን ጨምሮ ሌሎች የሳይበር ጥቃቶች “በኮምፒውተር ስርዓት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ እና ጥፋት ሊያስከትሉ የሚችሉ ሲሆኑ ወሳኝ መሠረተ-ልማቶቻችንን እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ተቋማቶቻችን ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ” ሲል ኔቶ በመግለጫዉ አትቷል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጦር ቃል-ኪዳን ድርጅቱ በበርካታ አጋጣሚዎች የሳይበር ጥቃት እንደ ወታደራዊ ጥቃት አካል አድርጎ እንደሚቆጥረው ሲያመለክት የነበረ ሲሆን አዲሱ ፖሊሲም ይህንን አቋም ማካተቱን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።