አልማ በህወሓት ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ

ነሃሴ 3/2013(ዋልታ) -የአማራ ልማት ማህበር አሸባሪው ትህነግ በፈጠረው ቀውስ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች የዕለት ደራሽ ድጋፍ አቀረበ፡፡

የማህበሩ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አራጋው ታደሰ በዋግ ህምራና ሰሜን ወሎ አስተዳደር ዞን የቆቦ፣ራያ፣አላማጣ እና ግዳን ወረዳ ነዋሪዎች በአሸባሪው ትህነግ ምክንያት ከሰላማዊ ኑሯቸው ተፈናቅለው ደሴና ወልድያ ከተማ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የማህበሩ ማናጅመንት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጭ የተደረገበት 327 ኩንታል የፊኖ ዱቄት ቦታው ድረስ በማጓጓዝ ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲውል ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ወር ጀምሮ የማህበሩ ሰራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸው አሸባሪውን ቡድን ተግባርና አስተሳስብ ለማምከን በሚደረገው ሀገራዊ ርብርብ ድጋፍ እንዲውል ወስነዋል፡፡

ትህነግ በፈጠረው ቀውስ የተፈናቀሉ ወገኞችን ለማቋቋምም ሆነ የአሸባሪውን ቡድን ተግባርና አስተሳሰብ ለማፅዳት የሚደረገውን የተቀናጀ የህዝብና የመንግስት ጥረት አልማ አባላቱንና ደጋፊዎቹን በማስተባበር ድጋፉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ከማህበሩ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አለሙ ይመር÷አልማ እያከናወነ ከሚገኘው ዘላቂ ማህበራዊ ልማት ጎን ለጎን በአሸባሪው ትህነግ የተፈናቀሉ የተወሰኑ ወረዳ ነዋሪዎችን ለማቋቋም ባበረከተው የዕለት ደራሽ ድጋፍ ሁነኛ የክልሉ ህዝብ አጋርነቱን አስመስክሯል ብለዋል፡፡