አመራሩ ከባለሀብቶች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል – አቶ አገኘሁ ተሻገር

 

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር

የካቲት 12 /2013 (ዋልታ) – አመራሩ በኢንቨስትመንት መስክ ከባለሀብቶች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እራሱን እንዲያዘጋጅ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር አሳሰቡ።

በኢንቨስትመንት ዘርፉ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አላማ ያደረገ የምክክር መድርክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተጀምሯል ።

ርዕሰ መስተዳደሩ በወቅቱ እንደገለጹት ሀገራዊ ለውጡ እንዲመጣ ለተደረገው ትግል መሰረታዊ መንስኤ ከሆኑት መካከል ፍትሃዊ የሆነ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ አለመኖርና የኢንቨስትመንት ፍሰት ክፍተቶች ተጠቃሽ ናቸው ።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ከለውጡ በኋላ በክልሉ በተሰሩ የሰላምና የማረጋጋት ስራዎች ለልማት እንቅፋት የማይሆን አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል።

በክልሉ አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ በተለያዩ ስጋቶች ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረው የኢንቨስትመንት
እንቅስቃሴ በፍጥነት እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል።

የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እያደገ ቢመጣም በየደራጀው ያለው አመራርና ባለሙያ ዘንድ የባለሃብቱን ጥያቄ መሰረት አድርጎ ውሳኔ የመስጠት ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን ርዕሰ መስተዳደሩ ጠቁመዋል።

ከቀበሌ እስከ ክልል ያለው አመራር የባለሃብቱን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ፈጣን ምላሽ እንዲያገኝ መዘጋጀት እንዳለበት አሳስበዋል።