ሐምሌ 06/2013 (ዋልታ) – አሜሪካ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የበቀል እርምጃዎችን አወገዘች፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይዝ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸመውን ማንኛውንም የበቀል ጥቃት ሊወገዝ ይገባል ብለዋል፡፡
ቃል አቀባዩ አሜሪካ ለግጭቱ በድርድር ላይ ለተመሰረተ ሰላማዊ መፍቴ የምታደርገውን ጥሪ እንደቀጠለች መሆኑን ተናግረው ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ የሆኑት ሁሉም አካላት በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አክለውም በተደራጁ ወታደራዊም ይሁን በደህንነት ኃይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመ ወይም ሊፈጸመ የሚችል ማንኛውንም የበቀል ጥቃት አጥብቀን እናወግዛለን ማለታቸውን አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
አሸባሪ ተብሎ በተወካዮች ምክር ቤት የተሰየመው ህወሓት በኤርትራዊያን ስደተኞች ላይ የበቀል እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የኤርትራው የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
ህወሓት በስደተኛ ጣቢያዎች ውስጥ ባሉ ንጹሃን ኤርትራዊያን ላይ ሳይቀር በበቀል ተነሳስቶ ጭፍጨፋ እየፈጸመ እንደሚገኝ ነው አቶ የማነ የገለጹት።