አምስተኛው የኢትየጵያና ስዊዘርላንድ የጋራ የፖለቲካ ምክክር ተካሄደ

ጳጉሜ 1/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ እና ስዊዘርላንድ ረዥም ዘመናት ያስቆጠረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በአዳዲስ የተመረጡ መስኮች በማስፋት የትብብሩን ጥልቀት ለማሳደግ የሚያስችል የጋራ የፖለቲካ ምክክር በአዲስ አበባ ተካሄዷል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ በምክክሩ ወቅቱ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን የጀመረው የሁለቱ አገራት ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቅሰው በተለይም በንግድ፣ በልማት ትብብርና በሰብዓዊ ድጋፍ ረገድ ስዊዘርላንድ ከአገራችን ጋር ያላትን አጋርነት አድንቀዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው በሰሜኑ አገራችን ክፍል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ የሰጡ ሲሆን ሕወሓት ጦረኛ ኃይል ሆኖ እንዲቀጥል መፈቀድ እንደሌለበት ተናግረዋል።
አያይዘውም በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት በትብብር መስራት እንደሚገባ፣ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ሂደት በሙሉ ልብ መደገፍ እንዳለበት፣ ተወዳዳሪ የሰላም ሂደቶች እንጀምር የሚሉ ወገኖች ከድርጊታቸው ተቆጥበው የተጀመረውን ጥረት ማገዝ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
የስዊዘርላንድ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሪ ዋልት በበኩላቸው ስዊዘርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ቦታ እንደምትሰጥ ጠቅሰዋል።
አገራቸው ከሰሃራ በታች ለሚገኙ የአፍሪካ አገራት ባዘጋጀችው ስትራቴጂ ኢትዮጵያን የበለጠ ትስስር ለማድረግ ከለየቻቸው ዘጠኝ “ባለ አንበሳ ኢኮኖሚ” አገራት መካከል አንዷ መሆኗን አንስተዋል፡፡
ስዊዘርላንድ እ.ኤ.አ ጥር 1 ቀን 2023 ጀምሮ ለሁለት ዓመታት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና የምታገለግል በመሆኑ ኢትዮጵያ በፀጥታው ምክር ቤት በነበረችበት ወቅት የነበራትን ተሞክሮ አካፍላለች፡፡
የስዊዝ ወገንም ለልምድ ልውውጡ ምስጋናውን ማቅረቡን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡