አምባሳደር ስለሺ በቀለ ከአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጋር ተወያዩ

ነሐሴ 4/2014 (ዋልታ) በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ከአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እና አባል ግሪጎሪ ሚክስ ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይታቸውም አምባሳደር ስለሺ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ለተጎጂዎች ለማድረስ የሚደረገው ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑንና አሁንም ስለሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ለውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡

በተጨማሪም በሀገሪቱ ስለተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች፤ ለሰላም ግንባታ እና ዴሞክራሲን ለማስፈን እተከናወኑ ስለሚገኙ ተግባራት እና ሌሎች ጉዳዮችም ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራት ከቀረጥና ኮታ እገዳ ውጪ ምርታቸውን ወደ አሜሪካ ገበያ ከሚያቀርቡበት ስምምነት (ከአጎዋ)  ውጭ ስለመሆኗ፤ ስለ ኤች አር 6600 እንዲሁም ኤስ 3199 ሰነዶች እና ስለ ወቅታዊ የአልሻባብ ትንኮሳ አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ ላይ የተጣለው የአጎዋ እገዳ እንዲነሳ እንዲሁም ሁለቱ ሰነዶች ውድቅ እንዲደረጉ አምባሳደር ስለሺ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት ከምዕተ አመት በላይ የዘለቀ እንደመሆኑ እሱን በሚጥን መልኩ ግንኙነቱን በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ኢነርጂ፣ ሰላም ግንባታ እና ደህንነት ላይ በጋራ መስራት እንደሚገባም አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት፤ የተናጠል የተኩስ አቁሙ፤   የብሔራዊ ምክክሩ እና የሰላም ግንባታ ረገድ እየተስተዋለ ያለውን  አዎንታዊ ለውጥ አድንቀዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራን ታሪካዊ ግንኙነት በንግድ እና ኢንቨስትመንት ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸው በሀገራቱ መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብ የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ለአምባሳደር ስለሺ ቃል መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡