አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የምክር ቤቱ ውሳኔ ለኢትዮጵያ ትርጉም የለሽ ነው አሉ

ታኅሣሥ 10/2014 (ዋልታ) የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ በኢትዮጵያ ላይ ምንም ዓይነት ትርጉም የሌለውና ኢትዮጵያ የማትቀበለው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ መብቶች ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ አንድን ሉኣላዊት አገር በመግፋትና በማስጨነቅ ለአገዛዝና ለበላይነታቸው እንዲመች የማድረግ አባዜ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ውሳኔው ኢትዮጵያ የማትቀበለውና ምንም ዓይነት ትርጉም የሌለው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮና የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ምርመራ አድርገው የምርመራ ውጤቱን ይፋ ማድረጋቸውን አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያም የማትስማማባቸው ነገሮች ቢኖሩም በሂደቱ ግን እንደምትስማማ ገልጻ የቀረቡትን የመፍትሄ ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ላይ እያለች የተጠራ ስብሰባ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ውሳኔውም አገሪቱ ላይ አላስፈላጊ ጫናና ወከባ ለመፍጠር ያለመ እንጂ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል፡፡

የጥምር ቡድኑ ያደረገውን ማጣራት ወደጎን ብለው ሌላ አጣሪ ቡድን ለማቋቋም መፈለጋቸው እነሱ ያልጀመሩትና ያልፈጸሙት ነገር ተቀባይነት እንደማይኖረው ለማሳየት ያደረጉት ጥረት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይህም የስውር ቅኝ አገዛዝ ለማድረግና ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።