በሕዳሴው ግድብና በፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶች መክሸፋቸው ተገለጸ

ሚያዝያ 25/2014 (ዋልታ) በሕዳሴው ግድብ እና በከፍተኛ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶች መክሸፋቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ገለጸ።

የአገሪቱን ሰላም እና ዕድገት በማይፈልጉ አገራት የሚደገፍ ድርጅት የሕዳሴው ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል በማቀድ “ብላክ ፒራሚድ ዋር” በሚል ስያሜ የሳይበር ጦርነት መክፈቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ይሁንና የጥፋት ዓላማ አቅደው ሲያሴሩ የነበሩት ሁሉ እንዳሰቡት ሕልማቸው ሳይሳካ ተጨናግፏል ብለዋል።

የፋይናንስ ተቋማት የሚጠቀሙባቸው እና እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ 37 ሺሕ ኮምፒውተሮችን ላይ ጥቃት በመፈጸም የሕዳሴው ግድብን ለማስተጓጎል እንደተሞከረም ገልጸዋል።

ጥቃቶቹም በኢንፎርሜሽን ደኅንነት አስተዳደር ጥብቅ ክትትል ምንም ጉዳት ሳያስከትሉ እንዲቋረጡ እና እንዲመክኑ መደረጋቸውን አስታውቀዋል።

የሕዳሴው ግድብ ኃይል ማመንጨት ከጀመረ በኋላ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚችል ይገመታል ያሉት ሹመቴ (ዶ/ር) ከዚህ በኋላም የሳይበር ምኅዳሩን በመጠቀም ግድቡ በአግባቡ ኃይል እንዳያመነጭ እና እንዲቆም ጥረት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል።

ለዚህም ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ተግባራዊ በማድረግ ከሕዳሴው ግድብ ግንባታ እና ቁጥጥር ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ግድቡን በተመለከተ ከአመራረት እስከ ግንባታ ዕቃዎች ማጓጓዣ የሚያጠቃልሉ ሥራዎች ላይ የሳይበር ምኅዳሩን በመጠቀም ከፍተኛ ክትትል ይደረጋልም ብለዋል።

በሕዳሴው ግድብ ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶች እስካሁን ምንም ዓይነት ጉዳት ሳያደርሱ እንዲመክኑ ቢደረግም አሁንም የፋይናንስ ተቋማት ላይ ተመሳሳይ ጥቃቶች እየተሰነዘሩ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ኢነርጂ ተቋማት ሁሉ ፋይናንስ ተቋማትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚደረጉ የሳይበር ጥቃቶች ዒላማ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

የሳይበር ጥቃቶችን ለመከላከል ሁልጊዜም አንድ እርምጃ ቀድሞ ማየት፣ ማቀድ እና መተግበር ያስፈልጋል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች ሰብረው መግባት ከቻሉ መዘዛቸው ብዙ እንደሆነ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የተቃጡት ጥቃቶች ቢሳኩ ኖሮ በፋይናንስ ተቋማት ላይ ብቻ ሳይሆን በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ችግር ያስከትሉ እንደነበር ገልጸዋል።

የፋይናንስ ተቋማቱ ከነዚህ ዓይነት ጥቃቶች ራሳቸውን ለመጠበቅና ለመከላከል አስፈላጊ የሚባሉ ዝግጅቶችን ማድረግ አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።