አሸባሪው ህወሓት የበላይነቴን አስቀጥላለሁ ካልሆነም ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ የሚል የሞኝ ዘፈን እየዘፈነ ነው – ሙስጠፌ መሀመድ

ጥቅምት 01/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ህወሓት የበላይነቴን አስቀጥላለሁ ካልሆነም ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ የሚል የሞኝ ዘፈን እየዘፈነ ነው ሲሉ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ።

አሸባሪው ህወሓት ሁለት ግልጽ ዓላማዎች እንዳሉት የገለጹት አቶ ሙስጠፌ፣ አንደኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ለእኔ ጥቅም የቆመ መንግሥት መምጣት አለበት የሚል እና እንዳለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን እንደፈለኳት የማልዘውራት ካልሆነ ደግሞ ትግራይ ትገነጠላለች የሚል ሁለተኛ አቋም ያራምዳል ብለዋል።

ይህንንም የሽብር ቡድኑ አላማ ካዘጋጃቸው ዶክሜንቶችና ከተግባሩ መረዳት ይቻላል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ እነዚህ የአሸባሪው ቡድን ዓላማዎችን ደግሞ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት የሚቀበላቸው አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ አንድነቷ ተጠብቆና ሰላሟ ሰፍኖ እንድትቀጥል ከተፈለገ በእኔ እምነት አሸባሪው ህወሓት መወገድ አለበት ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

በአሁኑ ጊዜ የህወሓት 27 ዓመታት የግፍ አገዛዝ ስርዓት እንዲቀጥል የሚፈልግ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሌለ ገልጸው፣ ትግራይን እገነጥላለሁ የሚለው ዓላማውም ከውጭ ኃይል ጋር ተባብሮ ኢትዮጵያን የማፍረስ ተላላኪነቱን የሚያረጋግጥ ማሳያ በመሆኑ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት እንደማይፈቅድለት ተናግረዋል።

ሁለቱም ዓላማዎቹ በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት በኩል ተቀባይነት ማግኘት ስለማይችሉና ከኢትዮጵያውያን ፍላጎት ውጪ ስለሆነ አሸባሪው የህወሓት ቡድን መወገድ አለበት ብለዋል።