አሸባሪው ሕወሓት በሕዝብ ላይ ይቅር የማይባል አሰቃቂ ግፍና በደል ፈፅሟል

ታኅሣሥ 3/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት በአማራ ክልል በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች በሕዝብ ላይ ይቅር የማይባል አሰቃቂ ግፍና በደል መፈጸሙን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
አሸባሪው ኃይል በደሴ ዩኒቨርሲቲ፣ በደሴና በቦሩ ሜዳ ሆስፒታሎች ላይ ያደረሰውን ውድመት ጎብኝተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉትም አሸባሪውና ወራሪው ኃይል የአገርና የሕዝብ ጠላት መሆኑን በተግባር አሳይቷል።
በአማራ ክልል በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች ሁሉ በዜጎች ላይ ግዲያ ከመፈፀም በተጨማሪ ሴቶችን በመድፈር ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ያሳደረ ሲሆን በምጣኔሃብት ለማዳከም የፈፀመው ዘረፋና ወድመትም መጠነ ሰፊ መሆኑን ገልጸዋል።
በፀጥታ ኃይሎች ጥምረት አከርካሪው የተሰበረው አሸባሪው የሕወሓት ወራሪ ኃይል ዳግም እንዳይነሳ ተደርጎ እየተመታ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ሕዝብ ከመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመተባበር አሸባሪው ሕወሓት የዘረፋቸውንና ያወደማቸውን ተቋማት መልሶ መገንባት አለበት ብለዋል።