አሸባሪው ሕወሓት በጭፍራ ግንባር ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑ ተገለጸ

ኅዳር 7/2014 (ዋልታ) – የመከላከያ ሰራዊት፣ አፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በጋራ በመሆን በጭፍራ ግምባር አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሱበት እንደሚገኙ የጭፍራ ግምባር ኮማንድ ፖስት አስታወቀ።

በአፋር ክልል የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የጭፍራ ግምባር የኮማንድ ፖስት አስተባባሪ አብዱ ሙሳ አሸባሪው ቡድን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየፈጸመ እንደሚገኝ አውስተዋል፡፡

የአፋር ህዝብ አንድነቱን ጠብቆ አሸባሪ ቡድኑን እየመከተ እንደሚገኝም ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአፋር ህዝብ ‘ዳጉ’ በተሰኘው የመረጃ መለዋወጫ ባህል አማካኝነት የአሸባሪ ቡድኑን እንቅስቃሴ የሚመለከቱ መረጃዎችን እንደሚለዋወጥ ጠቅሰው ይህም አሸባሪ ቡድኑን ለመመከት መልካም እድል ፈጥሯል ነው ያሉት፡፡

የአፋር ልዩ ኃይል ምክትል አዛዥ ምክትል ኮማንደር መሓመድ ሰናይ በበኩላቸው አሸባሪው ሕወሃት ውጊያ በከፈተባቸው ግምባሮች ሁሉም የአፋር ክልል የጸጥታ ኃይሎች ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት የአገር ሉዓላዊነትን እያስከበሩ ነው ብለዋል።

በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ የሚሊሻ አባላትም ከጸጥታ ኃይሉ ጎን ተሰልፈው አሸባሪውን እንዲመክቱ ጥሪ አቅርበዋል።