አሸባሪው ሕወሓት ከገባበት መውጫ አጥቶ በያለበት እንዲደመሰስ የተቀናጀ ዘመቻ እየተካሄደ – አለሙ ስሜ (ዶ/ር)

አለሙ ስሜ (ዶ/ር)

ኅዳር 15/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓት ከገባበት መውጫ አጥቶ በያለበት እንዲደመሰስ የተቀናጀ ዘመቻ እየተካሄደ ነው ሲሉ በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ

የጠላት ኃይል ዙሪያውን በእሳት ቀለበት ተከቦ እየተመታ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ ባደረገባቸው አካባቢዎች የሚያደርሰውን ጉዳት ለማስቆምና ቡድኑን ለማጥፋት የጸጥታ ኃይሉ የተቀናጀ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል ብለዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪው የሽብር ቡድኑና ተላላኪዎቹን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ለማጥፋት የተቀናጀ የአመራር ስምሪት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በዚህም ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጀምሮ ሁሉም ከፍተኛ አመራሮች ወደ ግንባር መዝመታቸውን ተናግረዋል።

አሸባሪው ሕወሓት በወረራ ከገባባቸው አካባቢዎች መውጫ አጥቶ በያለበት እንዲደመሰስ የተቀናጀ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከፍተኛ አመራሮች ወደ ግንባር የዘመቱት የመከላከያ ሰራዊቱን ስራ ለመተካት ሳይሆን ህዝብን በማስተባበር የሽብር ቡድኑ በየትኛውም አካባቢ መውጫ እንዳያገኝና ተመልሶ ወደ ተንቤን በርሃ እንዳያመልጥ ለማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ጠላትን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት በኢትዮጵያ ላይ የሚመጣን ማንኛውም ጥቃት በብቃት በመመከት ጠላትን አሳፍሮ መመለስ የሚችል አቅም መፈጠሩንም አረጋግጠዋል።

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ግርማ የሺጥላ በበኩላቸው የጠላት ሃይል ዙሪያውን በእሳት ቀለበት ተከቦ እየተመታ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዚህም ትግሉን በፍጥነት አጠናቆ ወደ ልማት መመለስ የሚያስችል የተደራጀና ራሱን ለመስዋዕትነት ያዘጋጀ የህዝብ ንቅናቄና አመራር መፈጠሩንም ተናግረዋል።

ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጥሪ ተቀብለው ወደ ግንባር መዝመታቸውን ጠቅሰው ኢትዮጵያን ለማዳን በቂ ዝግጅት ተደርጓል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።