አሸባሪው ሕወሓት ከፍተኛ ሽንፈት እየደረሰበት መሆኑ ተገለፀ

ኅዳር 2/2014 (ዋልታ) በባቲ አሳጊታ ግንባር ባለፉት ዘጠኝ ቀናት ከ20 ያላነሰ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረገው አሸባሪው ሕወሓት ከፍተኛ ኪሳራና ሽንፈት መከናነቡን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ አስታወቀ።

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዝ አዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን አገራዊ ሁኔታና የአዋጁን አፈፃፀም ገሞግሞ መግለጫ አውጥቷል።

ዕዙ በመግለጫው እንዳመለከተው ለሕብረተሰቡ የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ ምላሽ፣ የአዋጁን አፈጻጸምና ወታደራዊ ርምጃዎች በመገምገም  የተለያዩ ድሎች መመዝገባቸውን አረጋግጧል።

በባቲ- አሳጊታ ግንባር የጥፋት ኃይሉ ባለፉት ዘጠኝ ቀናት ከ20 ያላነሡ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን አድርጓል።

ሆኖም ጀግኖቹ የአፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀትና በንሥሮቹ የአየር ኃይል በመታገዝ፣ በጠላት ላይ ከፍተኛ ኪሣራ በማድረስ፣ ሁሉንም የማጥቃት እንቅስቃሴዎች አክሽፈው ወራሪው ሽንፈትን እንዲከናነብ ማድረጋቸውን ገልጿል።

ሚሌን ለመያዝ የነበረውን ፍላጎትም የሕልም እንጀራ እንደሆነበት አመልክቷል።

የአገር ሉኣላዊነትን ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ፣ የአማራ፣ የአፋርና የኦሮሚያ ክልሎች ሕዝብ የተደረገላቸውን አገራዊ ጥሪ በመቀበል ወደሁሉም ግንባሮች ከትቷል። ሌሎችም በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ ብሏል።

በትግራይ እና አፋር ክልል ወሰን ላይ ቢሶበር አካባቢ ጁንታው ዛሬ የከፈተውን አዲስ የማጥቃት ሙከራ፣ አንበሶቹ የአፋር ሚሊሻና ልዩ ኃይል የጠላትን አከርካሪ ሰብረው በዚህ ግንባር የመጣውን ጠላት አሳፍረው መልሰውታልም ሲል አክሏል።

በወረኢሉ ግንባር ለመስፋፋት አስቦ የተንቀሳቀሰው የጠላት ኃይል፣ በደቡብ ወሎ ሚሊሻና በጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት ተመትቶ መምከኑንም መግለጫው አስታውቋል፡፡

በአቀስታ ግንባር ለመንቀሳቀስ አስቦ የነበረው የሽብር ቡድን በአዊ፣ በምዕራብ ጎጃም፣ በምሥራቅ ጎጃምና በደቡብ ወሎ ሚሊሻ ተመትቶ ወደኋላ እንዲያፈገፍግ ተገድዷል ነው የተባለው።

በከሚሴ ግንባር ያሉት የመከላከያ ሰራዊት፣ በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና የሰሜን ሸዋ ዞኖች ሚሊሻዎች ባለፉት አምስት ቀናት ባደረጉት ተጋድሎ፣ ወረራውን በመቀልበስ፣ ወደ ፀረ ማጥቃት እንቅስቃሴ ተሸጋግረዋል።

በማይጸብሪ ግንባር የጥፋት ኃይሉ ተደጋጋሚ ፀረ ማጥቃት ቢያደርግም እንቅስቃሴው ከሽፏል።

በአጠቃላይ በአማራና በአፋር ክልሎች የክተት አዋጁን ተከትሎ በጠላት ላይ እየተወሰደ ያለው ርምጃ አመርቂ ሆኖ ተገኝቷል። ለዚህ መሠረቱ የሕዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ መነሣሣትና ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የፈጠረው ንቅናቄ መሆኑ ተረጋግጧል ሲልም የአስቸኳይ ጊዜ ዕዙ አሳውቋል።

እንደመግለጫው በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በሆሮጉድሩ እና በምሥራቅ ወለጋ አንዳንድ ወረዳዎች ላይ፣ ሰላማዊውን ሕዝብ በመግደልና ንብረት በመዝረፍ፣ የአሸባሪውን ሕወሓት ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀስ የነበረውን አሸባሪውን የሸኔ ቡድን በመደምሰስና ግብረ አበሮቹን በቁጥጥር ሥር በማድረግ፣ የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ የፌዴራል ፖሊስና የአገር መከላከያ የጋራ ጥምረት፣ ከፍተኛ ድል ተጎናጽፈዋል።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተደረገለትን አገራዊ ጥሪ በመቀበልና ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ይህ  አኩሪ ድል እንዲመዘገብ አድርጓል።

ለዚህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ የላቀ ምስጋናውን እያቀረበ የጀመረውን ሁለንተናዊ ተሳትፎ አጠናክሮ  እንዲቀጥል ጥሪ  አቅርቧል፡፡