አሸባሪው ቡድን በሴቶችና ህፃናት ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ ለማስቆም መተባበር እንደሚገባ ተገለጸ

መስከረም 25/2014 (ዋልታ) የሐረሪ ክልል ሴቶችና ህፃናት ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አሚና አብዱልከሪም አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአፋርና በአማራ ክልል በሴቶችና ህፃናት ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ ለማስቆም ተባብረን መስራት እንደሚገባ ገለጹ።

የክልሉ ሴቶችና ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ከክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ጋር በመሆን በአፋር እና በአማራ ክልል ለተፈናቀሉ ህጻናትና ሴቶች ከ1 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አበርክተዋል። ድጋፉም በክልሉ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል የተሰባሰበ ስለመሆኑ ተጠቁሟል።

ድጋፉን ያስረከቡት የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አሚና አብዱልከሪም አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአፋር እና በአማራ ክልል በሴቶችና ህፃናት ላይ እያደረሰ ያለውን ግድያ፣ አስገድዶ መድፈርና ማፈናቀል ለማስቆም ተባብረን መስራት ይገባል ብለዋል።

በተለይም በዚህ ጦርነት ምክንያት በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን በመጠቆም፤ ይህንን ችግር ለማቃለልም ከ1 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የምግብ፣ የአልባሳትና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማደረጋቸውን ገልጸዋል።

ድጋፉ የክልሉ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ከክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ እና የተለያዩ የሴት አደረጃጀት ጋር በጋራ በመሆን ከተለያዩ ማህበረሰብ ክፍል የተሰባሰበ መሆኑን አንስተው፣ በቀጣይ መሰል ተግባራት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የክልሉ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ቢሮ ምክትል ኃላፊ መፍቱሃ አልዩ በበኩላቸው፣ የአሸባሪው ትህነግ ቡድን ሀገር የማፍረስ ሴራን በመመከት የሀገራችንን አዲስ ምዕራፍና የብልጽግና ጉዟችንን እናረጋግጣለን ሲሉ መናገራቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።