አሸባሪው ትሕነግ በሱዳን ድንበር በኩል የሞከረውን የጥፋት እንቅስቃሴ ማምከን ተቻለ

የካቲት 03/2014 (ዋልታ) አሸባሪው የትሕነግ ቡድን ከሱዳን ድንበር ጋር ትስስር በመፍጠርና ከሌሎች ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ያደረገውን የጥፋት እንቅስቃሴ ማምከን መቻሉን የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አስታወቀ፡፡

የዕዙ ዋና አዛዥ ጄነራል ጌታቸው ጉዲና፣ የሽብር ቡድኑ በግንባር እያደረገ ያለውን ጥቃት ለማፋጠን ከሱዳን ድንበርና ከሌሎች ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር ያደረገውን ትስስር የምዕራብና የማዕከላዊ ጎንደር ብሎም የወልቃይት አካባቢ መስተዳድርና የፀጥታ ኃይሎች ከሰራዊታችን ጋር ጥምረት በመፍጠር ባደረጉት ወደር የሌለው ተጋድሎ ማምከን መቻሉን ገልፀዋል።

ቡድኑ እስካለ ድረስ ከጥፋት የማይመለስና ለእኩይ ዓላማ የተፈጠረ በመሆኑ ይህን የጥፋት ሰደድ ላይመለስ እስከወዲያኛው ማሰናበት ተገቢ እንደሆነም አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

እስካሁን የተሰሩ ሥራዎች በውጤታማነት የተቋጩት ጠንካራ የትብብርና የመደጋገፍ ባህል በመስፈኑ እንደሆነ የገለፁት ጄነራል መኮንኑ ከድል ማግስት ያሉ የትንሽነት አባዜዎችን በማኮስመን ትብብራችንን በደነደነ መሰረት ላይ ማስቀመጥ ይጠበቅብናል ማለታቸውን የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ጠቁሟል።

ጄነራል ጌታቸው እንደ አገር ትልቆች በመሆናችን እይታችንና ተግባራችን በትልልቅ አጀንዳዎች ላይ መሆን ይገባዋል ብለዋል።