አሸባሪዎቹን ትሕነግ እና ሸኔ በጋራ ለመዋጋት እንደሚሠሩ የሁለቱ ክልል ርዕሰ መሥተዳድሮች አስታወቁ

የካቲት 03/2014 (ዋልታ) የአማራና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በባሕር ዳር መክረዋል። በዚህም የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) የፀጥታ ጉዳይን የመፍታትና ለኢትዮጵያ አንድነት ለመቆም በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ገልጸዋል።

አሸባሪዎቹን ትሕነግ እና ሸኔ በጋራ ለመዋጋት ክልሎቹ በጋራ እንደሚሠሩም አስታውቀዋል።

ፀረ ሕዝብ የሆኑ ጠላቶችን በመደምሰስ ዜጎችን ማቋቋም እንዳለብንም ተግባብተናል ነው ያሉት።

የፅንፈኝነት እንቅስቃሴ ለመግታት መስማማታቸውን የተናገሩ ሲሆን ከአሁን በፊት የነበረውን ስምምነት ማደሳቸውንም ገልፀዋል።

ፅንፈኛ ኃይሎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመከፋፈል እየሠሩ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድር ይልቃል በጋራ ቆሞ ፅንፈኝነትን መዋጋት እንደሚገባም ተናግረዋል። ሕዝቡም ተረጋግቶ እና ሰክኖ በጋራና በአንድነት መቆም ይገባዋል ነው ያሉት።

የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ትልቁ ፈተና ፅንፈኝነት መሆኑን ገልጸው የአማራና የኦሮሚያ ክልል ሕዝቦች ኢትዮጵያን ለማስከበር ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

አሸባሪውን ሸኔ በጋራ ለመዋጋት እንደሚሠሩም አስታውቀው ከአሁን በፊት በነበሩ ጉድለቶች እና ጥንካሬዎች ላይ መምከራቸውንም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያን አንድነት በፅኑ መሠረት ላይ ማቆም እንዳለብን ተስማምተናልም ነው ያሉት።

ሁለቱ ርዕሰ መስተዳድሮች በአጎራባች አካባቢዎች በልማት እና በፀጥታ ጉዳይ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውንም አሚኮ ዘግቧል።