አሸባሪ ሕወሓትን በመደምሰስ መስዋዕትነት የከፈሉና ውድ አካላቸውን ያጎደሉ ጀግኖቻችን ተጋድሎ በታሪክ የሚወሳ ነው – ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ

ግንቦት 3/2014 (ዋልታ) አሸባሪው ሕወሓትን ለመደምሰስ በተካሄደው ጦርነት ውድ መስዋዕትነት የከፈሉና አካላቸውን ያጎደሉ ጀግኖቻችን የኅልውና ዘመቻ ድል በታሪክ የሚወሳ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ገለጹ።
ʺበሕግ ማስከበርና በኅልውና ዘመቻው የተከፈለ መስዋእትነት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ በዘመቻው የላቀ ሚና ላበረከቱ አካላት የእውቅና እና ምስጋና መርኃ ግብር በባሕር ዳር እየተሰጠ ነው።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ባስተላለፉት መልዕክት መላው የፀጥታ ኃይሎች በህግ ማስከበሩና በኅልውና ዘመቻው ደማቸውን በማፍሰስና አጥንታቸውን በመከስከስ ሀገር የማጽናት ኃላፊነታቸው ተወጥተዋል ብለዋል።
ይሁን እንጂ አሸባሪው ሕወሓት በወረራ በገባባቸው አካባቢዎች ንፁሀንን በመጨፍጨፍ፣ ሴቶችን በመድፈር ሃብት በመዝረፍና ሌሎች ክፍ ድርጊቶች መፈጸሙን አንስተዋል።
የሽብር ቡድኑ ይህን አሰቃቂ ድርጊት የፈፀመው ለዘመናት ተዛምዶና ተዋዶ የኖሩትን የአማራና የትግራይ ሕዝቦች አንድነት በመናድ አገር ለማፍረስ የያዘውን ግብ ለማሳካት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎችና የሌሎች ክልሎች የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት ቆራጥ የጋራ ተጋድሎ ቡድኑ ተበታትኖ እንዲመለስ መገደዱን አመልክተዋል።
በዚህ ጦርነት መስዋትነት ለከፈሉ፣ ውድ አካላቸውን ላጎደሉ ጀግኖቻችን ለዛሬው የመጀመሪያው የኅልውና ዘመቻ ድል ስላበቁን በታሪክ የሚወሳ መሆኑን ገልፀዋል።
አሸባሪ ቡድኑ አሁንም ሀገር የመበተን ሕዝብን የማሰቃየት ክፉ ሴራውን ዳግም ለመፈፀም እየተነሳሳ መሆኑን ጠቅሰው መላ ኢትዮጵያውያን በተባበረ የጀግንነት ክንዳቸው ህልሙን በማምከን የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) በበኩላቸው የሽብር ቡድኑን በአንድነት ተሰልፈን ባደረግነው ቆራጥ ተጋድሎ የሀገራችን አንድነትና የሕዝባችን ደኅንነት መጠበቅ ችለናል ብለዋል፡፡
በቀጣይም አሸባሪው ቡድን ለመፈፀም ያሰበውን ወረራ ቀድመን በማክሸፍ የሀገራችን አንድነት ተጠብቆ እንዲዘልቅ የጀመርነውን አብሮነት አጠናክረን መቀጠል አለብን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።