አቢሲኒያ ባንክ ከ4 የግል የማይክሮፋይናንስ ተቋማት ጋር የብድር ስምምነት ተፈራረመ

ሐምሌ 13/2013 (ዋልታ) – አቢሲኒያ ባንክ ከ4 የግል የማይክሮፋይናንስ ተቋማት ጋር የ600 ሚሊየን ብር የብድር ስምምነት ተፈራረመ።

ስምምነቱ በአዲሱ የብሔራዊ ባንክ ተንቀሳቃሽ የብድር ዋስትና ምዝገባ መመሪያ ማዕቀፍ የተከናወነ ነው ተብሏል።
መመሪያው ባንኮች የማበደር አቅም ቢኖራቸውም ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት በቂ ብድር ካለማቅረብ ጋር ተያይዞ ሲነሳ የቆየውን እና የፋይናንስ እጥረት የፈጠረውን ችግርም ይፈታል ተብሏል።
ባንኩ የብድር ስምምነቱን የተፈራረመው ‹ዳይናሚክ›፣ ‹ሀርቡ›፣ ‹መተማመን› እና ‹ንስር› ከተባሉ የማይክሮ ፉይናንስ ተቋማት ጋር ነው፡፡
ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመሪያ በግብርና ሥራ ለተሰማሩ ግለሰቦች፣ ለሕብረት ሥራ ማህበራት እና ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት የብድር አገልግሎት መስጠትን ያስችላል ተብሏል።
ብድሩ ለተፈለገው ዓላማ እንዲውል ለማድረግ ፣ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት እና በጅምላ ብድሮች የሚሰጥበት የብድር ተቋም ለማደራጀት ያግዛል ተብሏል።
አቢሲንያ ባንክ ለተቋማቱ ከዚህ በፊት ጥብቅ የነበረውን የዋስትና መስፈርቶች ቀለል እንዳደረገላቸውም ተነግሯል።
መመሪያው ከገንዘብ ምንጮች የሚደረግ ድጋፍን በመክፈት ሥርዓት ያለው የአፈፃፀም ሂደትን የሚያበረታታ የጅምላ ብድር መድረክ መፍጠሩን ተናግሯል።
ስምምነቱ በማስተርካርድ ፋውንዴሽን ያንግ አፍሪካ ወርክስ ስትራቴጂ መሠረት የተፈፀመ መሆኑ ነው የተነገረው።
(በሳራ ስዩም)