አብን የሀገርን ሉአላዊነትና ደኅንነትን በሚመለከት የማያሻማ አቋም እንዳለው ገለጸ

ሰኔ 28/2013 (ዋልታ) – የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሀገርን ሉአላዊነትና ደኅንነትን በሚመለከት የማያሻማ አቋም እንዳለው ገለጸ፡፡

የአብን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰኔ 26 እና 27 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይት ማድረጉን በመግለጽ፣ 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫና የብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮችን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ንቅናቄው በተለይ በሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት፣ በህዝብ ጥቅምና ክብር እንዲሁም በሀገረ መንግስቱ ቀጣይነት ረገድ ግልጽና የማያሻማ አቋም እንዳለው አስታውቋል፡፡

በመሆኑም አብን ማዕከላዊ መንግስትና በየደረጃው ያሉ መንግስታዊ አካላት ሀገሪቱ ከተደቀነባት የህልውና አደጋ ለመታደግ እንዲቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የብሔራዊ ደኅንነት እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል፡፡

መንግስት የሀገሪቱን እና የዜጎችን ሰላም፣ ደህንነት፣ ጥቅምና ክብር በማስጠበቅ ረገድ የሚታዩ ክፍተቶች እየተስተዋሉ ስለመሆኑም ነው የገለጸው፡፡

ራሱን የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር (ትህነግ) ብሎ የሚጠራው የሽብር ቡድን ተመልሶ በማንሰራራት በብሄራዊ ደህነታችን ላይ ተቀዳሚ አደጋ ሊሆን በቅቷል ሲልም ነው የንቅናቄው የሥራ አስፈፃሚ የግምገማ አቋሙን ያሳወቀው፡፡ ይሁንና መንግሥት ሕወሓት ለሀገር ሥጋት የሚሆንበት ደረጃ ላይ አለመሆኑን እየገለፀ ይገኛል ብሏል፡፡

በሌላ በኩል በምርጫ ሂደቱ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎችን ተመልክቻለሁ ያለው አብን፣ ምርጫ ቦርድ ከነውስንነቱ፤ ዜጎችም ለመምረጥ የሄዱበት ርቀት የሚደነቅ መሆኑን በመግለጫው አንስቷል፡፡

በመሆኑም ንቅናቄው የመራጩን ድምጽ በማክበር የህዝቡን ሀቀኛ ውሳኔ እንደሚቀበል አስታውቋል፡፡

በ6ኛ አገራዊ ምርጫ ፓርቲው እንቅስቃሴ ባደረገባቸው በአማራ ክልልና ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች 510 የሚሆኑ እጩዎችን እንዳሳተፈ ተገልጿል፡፡

(በሰለሞን በየነ)