አቶ ንጉሡ ጥላሁን ከአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ

አቶ ንጉሡ ጥላሁን

ሐምሌ 16/2013(ዋልታ) – የኢፌዴሪ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ንጉሡ ጥላሁን በአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ቤት ደንፎርድ ከተመራ የልዑካን ቡድን ጋር ተወያዩ።

አቶ ንጉሡ ጥላሁን በውይይታቸው ወቅት የአፍሪካ ልማት ባንክ በኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ እያደረገ ላለው ያልተቋረጠ ድጋፍ አመስግነዋል።

በቀጣይ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለው ስትራቴጂካዊ አጋርነት መስፋት አለበት ያሉት አቶ ንጉሡ የአፍሪካ ልማት ባንክ ኮሚሽኑ ለሚሰራቸው ስራዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንት ቤት ደንፎርድ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች የሥራ ዕድልን ለማመቻቸት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጋር በቅንጅት መሥራታቸውን አድንቀዋል።

ተወያዮቹ አጋርነቱ በፍጥነት ወደ ትግበራ ደረጃ እንዲሸጋገር በመስማማት ውይይቱን ማጠናቀቃቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።