ጥቅምት 20/2017 (አዲስ ዋልታ) በሀገር በቀል ፈጠራ አውድ ውስጥ ማህበረሰብን መሠረት ያደረጉ የመረጃ ዘዴዎችን እና አካባቢያዊ ዕውቀቶችን ከዲጂታል ዘዴዎች ጋር ማወዳጀት ለስታቲስቲክስ ልማት መሰረታዊ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የአፍሪካን የፈጠራ አቅም ለስታቲስቲክስ ዕድገት መጠቀም” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በተጀመረው ዘጠነኛው የአፍሪካ ስታቲስቲክስ ኮሚሽን መክፈቻ መርኃ ግብር ላይ ተገኝተዋል።
በዚህ መድረክ ስታቲስቲክስን ዘመናዊ ለማድረግ እና ያሉ የአሰራር ስርዓቶችን ለማዘመን እንዲሁም እንደ አህጉር ያሉንን ጠንካራ ጎኖች እንዴት በጋራ መጠቀም እንደምንችል የምንመክርበት ነው ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
መረጃ የሕዝብ ሀብት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሀብት ደግሞ በአግባቡ እና በተገቢ መንገድ ለመጠቀም ዘመናዊ የስታቲስቲክስ ስርዓቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
በመሆኑም የአፍሪካ መንግስታት የአህጉሪቷን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለመገንባት በሚደረገው በዚህ ትልቅ ሃሳብ ላይ ቁርጠኛ ልንሆን ይገባናልም ብለዋል፡፡